በኢትዮጵያ የዳልጋ ከብቶችን ምርታማነት ለመጨመር ባለፉት አራት ዓመታት ሰፊ የማዳቀልና የዝርያ ማሻሻል ስራዎች መከናወናቸውን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ከዚህ ቀደም የአገር በቀል ላሞች በቀን ይሰጡት የነበረው 1.5 ሊትር ወተት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ይህንን ለመቀየር ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር መደረጉን የተናገሩት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ናቸው።
ለማዳቀል ስራው ወሳኝ የሆነውን ፈሳሽ ናይትሮጂን ለማምረት በወላይታ ሶዶ፣ በነቀምቴ፣ በባህር ዳርና በአሶሳ በሰዓት 40 እና 50 ሊትር የሚያመርቱ ማሽኖች ተተክለው ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በየዓመቱ ይሰለጥኑ የነበሩ የሚያዳቅሉ ቴክኒሻኖች ቁጥር ማደጉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህም በየዓመቱ የሚወለዱ የተሻሻሉ ጥጆች ቁጥር 2 ሚሊዮን መድረሱንና ይህም የወተት ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።
በአራት ዓመታት ውስጥ በሌማት ትሩፋት የእንስሳት ውጤቶች ምርታማነት በእጥፍ መጨመሩን የተናገሩት ዶ/ር ፍቅሩ፣ መርሃ ግብሩ የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት አልሞ የተነሳ ነው ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ በወተት ምርት በኩል በቤዝ ላይን የተያዘው 7.1 ቢሊዮን ሊትር ምርት ዘንድሮ ወደ 15.7 ቢሊዮን ሊትር አድጓል።
በተመሳሳይ የእንቁላል ምርት ከ3.2 ቢሊዮን ወደ 11.7 ቢሊዮን ሊያድግ ችሏል ያሉ ሲሆን፣ ይህ ስኬት የተመዘገበው በዘርፉ የታዩ የአሰራርና የቴክኖሎጂ ለውጦችን ተከትሎ መሆኑንና መርሃ ግብሩ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
አዲስዓለም አበበ
ሐምሌ 02/2018 ዓ.ም
