የወረቀት አውሮፕላን አጥፎ መስራት ማንኛውም ሰው ሊያደርገው ከሚችላቸው እጅግ ቀላል ነገሮች መሀል አንዱ ቢሆንም ይህ በተማሪዎች የተሰራው የዓለማችን ትልቁ የወረቀት አውሮፕላን ፈጽሞ ቀላል የሚባል አይደለም።
ከተለያዩ እና በርካታ ረጃጅም ወረቀቶች እና በርካታ ሊትር ሙጫ ብቻ የተሰራው ይህ ግዙፍ አካል 7 ሜትር ርዝመት እና 20.04 ሜትር የክንፍ ስፋት ያለው ሲሆን፤ ክብደቱም 28.49 ኪሎ ግራም ይመዝናል።
አውሮፕላኑ ምንም እንኳን ግዙፍ መጠንና ከባድ ክብደት ቢኖረውም፤ በጊነስ የዓለም ክብረ ወሰን ደንብ መሰረት እውቅና ለማግኘት በአንድ ሰው እጅ ብቻ ተወርውሮ ቢያንስ 15 ሜትር ርቀት በአየር ላይ መንሳፈፍ አለበት።
ይህ ክስተት ከሚወራው በላይ በተግባር ከባድ ቢሆንም ከኢካሩስ ፕሮጀክት በስተጀርባ ያሉ ተማሪዎች የአውሮፕላኑን መረጋጋት፣ ጥንካሬ፣ ክብደትና የበረራ ሳይንስ ህጎችን ለማስተካከል በከፍተኛ ጥንቃቄ ለወራት ሰርተዋል።
ቡድኑ ውጤታማ ንድፍ ላይ ለመድረስ ባደረገው የወራት ሙከራ በአጠቃላይ 300 ኪሎ ግራም ያህል ወረቀት እና 60 ኪሎ ግራም ሙጫ ተጠቅሟል።
የቀድሞው ክብረ ወሰን ተይዞ የቆየው እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ የጀርመኑ ብራውን ሽዋይግ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ቡድን 5 ሜትር ርዝመት፣ 24 ኪሎ ግራም ክብደት እና 18 ሜትር የክንፍ ስፋት ያለውን የወረቀት አውሮፕላን 18 ሜትር ያህል ርቀት ማብረር ችሎ በነበረበት ወቅት ነበር።
ይህ ክብረ ወሰን ከመመዝገቡ ከአንድ ወር በፊት፣ የቻይናውያን የተማሪዎች ቡድን በሪሞት መቆጣጠሪያ በሚሰራው የዓለማችን ትልቁ የወረቀት አውሮፕላን አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ማስመዝገባቸው የሚታወስ ነው።
ሀና ሰይፉ
ሐምሌ 03/2018 ዓ.ም
