በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እና በክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ስልታዊ አጋርነት የተመሰረተው “ምቹ” የዲጂታል ብድር አገልግሎት፣ በአራት ዓመታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማሰራጨት ታሪካዊ ስኬት ማስመዝገቡን አስታወቀ። አገልግሎቱ ይህንን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ያሰራጨው በ3.2 ሚሊዮን የባንክ ሂሳቦች አማካኝነት በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ተጠቃሚዎች ነው።
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደርቤ አስፋው እንደገለጹት፣ ይህ ስኬት ባንኩ ማህበረሰቡን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማብቃትና የሰዎችን ህይወት ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። አቶ ደርቤ አክለውም፣ ከምቹ የብድር ተጠቃሚዎች መካከል ከ76.5 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመው፣ ይህም አገልግሎቱ ቀደም ሲል የፋይናንስ እድል ባላገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም በሴት ስራ ፈጣሪዎች ዘንድ ያለውን ከፍተኛ ተመራጭነት ያሳያል ብለዋል።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘውን የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት የገነባው የክፍያ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙኒር ዱሪ በበኩላቸው፣ ቴክኖሎጂው ከመደበኛው የባንክ አሰራር ውጪ የነበሩትን እንደ ባለሱቆች፣ ነጋዴዎችና አነስተኛ አምራቾችን ለመጀመሪያ ጊዜ የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል።
በመላው ሀገሪቱ ያለማቋረጥ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጠው “ምቹ”፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች የብድር አማራጮችን እያቀረበ ይገኛል በ”ምቹ ዋቢ” እስከ 300,000 ብር፣ በ”ምቹ ጉያ” የንግድ ፈቃድ ለሌላቸው እስከ 15,000 ብር፣
በ”ምቹ ኪያ” የንግድ ፈቃድ ለሌላቸው ሴቶች እስከ 5,000 ብር፣ ፈቃድ ላላቸው ደግሞ እስከ 75,000 ብር ድረስ ያበድራል።
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ በፈጠራ የታገዙ የዲጂታል ፋይናንስ አማራጮችን በማስፋፋት የሀገሪቱን አካታች የኢኮኖሚ እድገት የመደገፍ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሐምሌ 07/2018 ዓ.ም
ቀዳሚው ከማስያዣ ነጻ የዲጂታል ብድር “ምቹ” የ60 ቢሊዮን ብር ብድር ስኬት አስመዘገበ፤ የብድሩ ተጠቃሚዎች 76 በመቶው ሴቶች ናቸው
