በአዲስ አበባ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ከ140 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ የሕግ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ በራዳር እና በጂፒኤስ ቴክኖሎጂ የታገዘ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የትራፊክ ደንብ የተላለፉ ከ140 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታወቀ።

ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ ባሽከረከሩት ላይ መሆኑም ተነግሯል።

ባለስልጣኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፤ በበጀት ዓመቱ ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ በራዳር የተመዘገቡ 122 ሺህ 99 አሽከርካሪዎች ላይ የሕግ እርምጃ ተወስዷል።

ከዚህ በተጨማሪም የመጠጥና አደንዛዥ እፅ ወስደው ሲያሽከረክሩ የተገኙ 3 ሺህ 356 አሽከርካሪዎች በደንብ መተላለፍ ተጠያቂ መደረጋቸው ታውቋል።

የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ገነት ዲባባ እንደገለጹት፤ ቁጥጥሩ የደህንነት ቀበቶ ሳያስሩ ማሽከርከርንና የሞባይል ስልክ አጠቃቀምን ያካተተ ነበር።

በዚህም የደህንነት ቀበቶ ሳያስሩ ወይም የተሳፋሪዎችን ደህንነት ሳያረጋግጡ የተንቀሳቀሱ 4 ሺህ 471፣ እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ስልክ እያነጋገሩ ያሽከረከሩ 10 ሺህ 334 አሽከርካሪዎች መቀጣታቸው ተገልጿል።
በሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ላይ በተደረገው የጂፒኤስ እና የአካል ቁጥጥርም፤ የጭንቅላት መከላከያ ኮፍያ (ሄልሜት) ሳያደርጉና ተያያዥ ደንቦችን በመጣስ የተገኙ 1 ሺህ 146 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተነግሯል።

ይህ በቴክኖሎጂ የታገዘ የቁጥጥር ስራ የመንገድ ተጠቃሚዎችን ደህንነት ከመጠበቅና በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚጠፋውን ሕይወትና ንብረት ከመታደግ አንጻር ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ባለስልጣኑ አስታውቋል።

ልዑል ወልዴ

ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *