ኢትዮጵያ በየብስና በአየር ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ መንገደኞች ላይ የምታደርገውን የድንበር ተሻጋሪ በሽታዎች ቁጥጥር ስርዓት ማዘመኗን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል።
ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ በአየር መንገድና በ16 የየብስ መግቢያ ኬላዎች በኩል በመጡ ከ7 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ላይ ጥብቅ የጤና ቁጥጥር ተደርጓል ያሉት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ናቸው።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተመሰረተበትን 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ለጋዜጠኞችና ለኢንስቲትዩቱ ባልደረቦች ገለፃ በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በንግግራቸው በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት ከ20 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የሚያጓጉዝ በመሆኑ፣ ተላላፊ በሽታዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የዓለም ጤና ድርጅት ደንብን መሰረት ያደረገ የ24 ሰዓት የክትትል ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
ይህ የጤና ደህንነት ስራ የሀገሪቱን ህዝብ ከዓለም አቀፍ የጤና ስጋቶች ለመጠበቅ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲስዓለም አበበ
ሐምሌ 08/2018 ዓ.ም
