የአሜሪካ ጥቃት ሰባት ሰዎችን መግደሉን ኢራን ገለጸች

አሜሪካ ለስድስተኛ ተከታታይ ምሽት በኢራን ላይ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ቴህራን በርካታ ሰዎች መሞታቸውን የዘገበች ሲሆን፥ ጥቃቱ የሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ ያነጣጠረ ነበር ተብሏል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ ጥቃቱ «የኢራንን ወታደራዊ አቅም ለማዳከም» የተደረገ ጥረት ነዉ ብሏል፡፡

እነዚህ ጥቃቶች ሁለቱ ሀገራት ባለፈው ወር የተፈራረሙት ጊዜያዊ ስምምነት አደጋ ላይ መውደቁን ያሳያሉ።

የአሜሪካ ወታደራዊ ክፍል በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ የእገዳ ጥሰት የሞከሩ ሶስት የንግድ መርከቦችን አቅጣጫ ማስቀየሩን እና አንዷን መርከብ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን አስታውቋል።

በሌላ በኩል እንደ ኳታር፣ ዮርዳኖስ እና ባህሬን ያሉ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት የመሠረተ ልማት ጥበቃቸውን እና ወታደራዊ ዝግጁነታቸውን እያጠናከሩ ነው።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጦር በአህቫዝ ከተማ ለሚገኝ የሕፃናት ካንሰር ሆስፒታል መፈናቀል ምላሽ ለመስጠት በባህሬን በሚገኝ የአሜሪካ አየር ኃይል ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

የኢራን ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል መሐመድ አክራሚኒያ የአሜሪካ ጥቃቶች ከቀጠሉ የኢራን እርምጃ «ወደ አዳዲስ አካባቢዎች እንደሚስፋፋ» አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካ ኢራን ወደ ድርድሩ እንድትመለስ ስትፈልግ፥ ኢራን ደግሞ አሜሪካ መጀመሪያ እገዳውን እንድታነሳ ትፈልጋለች።

የዋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮሊን ሌቪት፤ ትራምፕ ኢራንን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ነገር ግን ሁልጊዜ ለዲፕሎማሲ ክፍት መሆናቸውን ገልጸው፥ መርከቦች ላይ የሚሰነዘር ጥቃትን ግን እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን በአሁኑ ወቅት ከዋሽንግተን ጋር ለመነጋገር ምንም ዓይነት እቅድ እንደሌለውና ትኩረቱ ሀገሪቱን መከላከል ላይ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።

ሳራ ዮሐንስ

ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *