አሜሪካ ጥቃቱ በባህረ ሰላጤው የሚያልፉ የንግድ መርከቦችን የሚያጠቁ የኢራን ወታደራዊ አቅሞችን፣ የኮማንድ ማዕከላትን እና የሚሳኤል ቦታዎችን ለማዳከም ያለመ መሆኑን ገልጻለች።
በአጸፋው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጦር በዮርዳኖስ እና በኩዌት በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ በሚሳኤል እና በድሮን ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተገደሉት ሶስት ወታደሮች ክብር ሲባል ኢራንን በጣም በጠንካራ ሁኔታ እየመቱ መሆኑን ገልጸው፤ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ሊኖራት አይችልም ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው ዋሽንግተን አሁንም ለዲፕሎማሲ ክፍት መሆኗን ገልጸዋል።
ዋሽንግተን በኢራን ወደቦች ላይ የባህር ኃይል እገዳ እየጣለች ሲሆን፥ የኢራን ጦር ደግሞ ህግ የሚጥሱ መርከቦችን ኢላማ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦች መፈንዳታቸውን የገለጸው የኢራን ጦር፥ የአሜሪካ ዘመቻ እስከቀጠለ ድረስ አካባቢው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ሆኖ እንደሚቆይ አስጠንቅቋል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ደግሞ የስድስት መርከቦችን አቅጣጫ ማስቀየሩን ገልጿል።
በየካቲት 28 የተጀመረው ይህ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገ ሲሆን፥ በዓለም አቀፍ የኢነርጂ አቅርቦት እና በዋጋ ግሽበት ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
ሳራ ዮሐንስ
ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም
