የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን በበኩሉ የታሸገ ነዳጅ እሽጉ ሳይፈታ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ማድረግ የሕግ ግዴታ ሲሆን፣ በነዳጅ ላይ የሚፈጸም ቅሸባ በኢትዮጵያ የነዳጅ ንግድና ስርጭት ሕግ መሠረት ከባድ ወንጀል ተብሎ ሊቀጣ ይገባል ይላል።
በዚህ አመት ግንቦት ወር ጀምሮ እስከ ሰኔ መጨረሻ ባለዉ ጊዜ የአምስት ተሽከርካሪዎች መወረሱን ሪፖርት እንደተደረገለት የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማህበር አሳዉቋል።
የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ሌብነት እያበረታታን አይደለም፤ ሆኖም በሀገሪቱ አንዳንድ ክልሎች ባሉ የመንግስት አካላት የነዳጅ ቅሸባ ሲደረግ ተገኝቷል እየተባለ የተጫነው ነዳጅ ኮንትሮባንድ ነዉ በሚል እየተወረሰ መሆኑ ሰርተን የማንከፍለዉ እዳ ዉስጥ ከቶናል ብለዋል።
ባለንብረቶች በህጋዊ መንገድ ቀረጥ ተከፍሎ እየገባ ያለ ነዳጅ ኮንትሮባንድ የሚሆንበት አግባብ በሌለበት ህጋዊ መሠረትን ሳይጠብቁ መዉረስ አይገባም ይላሉ።
ኢትዩ ኤፍም በጉዳዩ ዙሪያ ባለንብረቶችን አነጋግሯል።
አቶ የማነ ፀጋዬ የተባሉ ባለንብረት ከሶስት ወር በፊት አዋሽ አርባ አካባቢ ነዳጅ ጭኖ ቢጓዝ የነበረን ተሽከርካሪ አሽከርካሪዉ ነዳጅ ሲቀሽብ ተገኝቷል በማለት ነዳጁን ሰመራ ላይ በማራገፍ ነዳጁን ከነተሽከርካሪዉ እንደተወረሰ ያለምንም የፍርድ ቤት ዉሳኔ በደብዳቤ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።
ባለንብረቱ አሁን ላይ ባለእዳ የሆኑበትን ክፍያ ለመክፈል የእርዳታ እና ድጋፍ ማሰባሰቢያ እየጠየቁ እንደሚገኝ የተመለከትን ሲሆን የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማህበር ጉዳዩን ከክልሉ እስከ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን በመዉሰድ ለማነጋገር ሙከራ ተደርጓል ተብሏል።
አቶ ጌትነት ማህመድ የኢትዩጵያ ፈሳሽ ጭነት ማህበር ምክትል ኘሬዝዳንት የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን እና ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስርን ለማነጋገር እንደተሞከረ ነግረዉናል።
ለዚህ ምን ምላሽ እንደተሰጠ ሲገልፁም” ነዳጅ እጥረት በተፈጠረ ሰሞን የተቋቋመዉ ኮማድፖስት ዉረሱ ብሏቸዋል ፤ ምን ማድረግ አንችልም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዉናል” ብለዋል።
ሌላኛዉ ባለንብረት አቶ ዳኛቸዉ አበበ ይባላሉ። ተሽከርካሪዎች እየተወረሱ እንደሚገኙ በመግለፅ አሽከርካሪዎች አጥፍተዉ ሲገኙ በጥፋት እነሱን መጠየቅ ሲገባ ለሀገር ጥቅም ሊዉል የተጫነን ነዳጅ እና ተሽከርካሪ መዉረስ ለወረሹ አካል ሌብነትን ማበረታታት ነዉ ይላሉ።
ሲቀሽብ ተያዘ የተባለዉን አሽከርካሪ በነፃ ለቆ ተሽከርካሪ መዉረስ ነገም ለተመሳሳይ ጥፋት አሽከርካሪን መጋበዝ እና ባለንብረትን ባለእዳ መድረግ ነዉ ብለዉናል።
ለኢትዩ ኤፌም ሀሳባቸዉ የሰጡት ሌላኛዉ ግለሰብ አቶ ዘላለም ነጋሲ ናቸዉ። ነዳጅን ኮንትሮባንድ ነዉ በሚል መያዝ ህጋዊ አይደለም ይላሉ። ይህንንም ሲያስረዱ “ነዳጅን መንግስት ሁሉን ነገር ከፍሎ እስከ ጅቡቲ ድረስ ያመጣዉ ነዉ። ይሄን ቀሽቦ የተገኘ አሽከርካሪ በእምነት ማጉደል ወንጀል መጠየቅ ሲገባ ኮንትሮባንድ ነዳጅ በሚል ተሽከርካሪ ከነነዳጁ መዉረስ ኮንትሮባንድ ወንጀል የሚለዉ መረዳት እንዳልቻሉ ያሳያል” ብለዋል
ሲቀጥሉም”ነዳጅን ኮንትሮባንድ ማለት ምን ማለት ነዉ? የጉምሩክ ኮምሽን በየክልሉ ሀላፊነት ለሰጣቸው አስፈጻሚዎች በቂ ግንዛቤ መስጠት ይገባዋል። ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም በአንድ መስሪያ ቤት ሀላፊ ትእዛዝ ንብረት መዉረስ ህገመንግስቱ የሰጠዉን መብትን መጣስ ነዉ” ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማህበር ዋና ኘሬዝደንት አቶ ፀጋ አሳመረ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡን ማብራሪያ ሌብነት እና ኮንትሮባንድ መለየት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ።
ቀረጥ የተቀረጠበትን ነዳጅ ሲቀሸብ ተገኝቷል በሚል ኮንትሮባንድ ብሎ መዉረስ አግባብ አይደለም በሚል ለሚመለከተዉ አካል እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር በደብዳቤ አሳዉቀናል ብለዋል።
“አንዳንድ ጊዜም ተሽከርካሪዎቹ አንድ ሺህ ሊትር ቀድተዉ ከሆነ ግማሹ ተሳቢዉ ላይ ነዉ የሚደረገዉ። ከዛ ከተሳቢዉ ላይ ወደ መኪናው ሲገለብጡ ነዉ የሚይዟቸዉ ይሄ አይነቱ አሰራር ያለ ነዉ ። ይሄን እነሱ ቅሸባ ነዉ የሚሉ እንደዋዛ ሊባል አይችልም”ሲሉም አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መሠለች ወዳጆ የታሸገ ነዳጅ እሽጉ ሳይፈታ እንዲደርስ ይፈልጋል ይላሉ ። ቅሸባዉ ወንጀል ነዉ መባል ያለበት ሲሉ ይገልፃሉ።
የታሸገ ነዳጅ እሽጉ ሳይፈታ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ማድረግ የሕግ ግዴታ ሲሆን፣ በነዳጅ ላይ የሚፈጸም ቅሸባ በኢትዮጵያ የነዳጅ ንግድና ስርጭት ሕግ መሠረት ከባድ ወንጀል ተብሎ ሊቀጣ ይገባል። በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ አቅርቦት እና ስርጭት መሪ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መሠለች ወዳጆ እንደገለፁት፣ የነዳጅ እሽግ ሳይፈታ ለተጠቃሚው መድረስ አለበት።
ባለሥልጣኑ በድንገተኛ ፍተሻ በመቅጃ ማሽኖች (ዲስፔንሰር) ላይ ትክክለኛ ያልሆነ ልኬትና ቅሸባ በፈጸሙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ የማገጃ እርምጃዎችን የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና ግብይት ወጥነትን ለመፍታት እና ቅሸባን ለመከላከል በዲጂታልና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየተዘረጋ ይገኛል ብሏል።
ቁምነገር አየለ
ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም
