በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚስተዋሉ የአቅም፣ የኢንቨስትመንት እና የፖሊሲ ትስስር ማነቆዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል አዲስ የስምምነት ምዕራፍ በዛሬው እለት ተከፍቷል።
የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር (EREDA) እና ዶክሳ ቢዝነስ ትሬዲንግ፣ የሀገር ውስጥና የአህጉር አቀፍ የቢዝነስ ትስስሮችን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ሁለት ስትራቴጂያዊ የመግባቢያ ሰነዶችን በይፋ ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ አልሚዎችን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ የፖሊሲ አውጪዎችን እና የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችን በአንድ ወጥ መድረክ በማገናኘት፣ እስካሁን በዘርፉ ሲታይ የነበረውን የተቆራረጠ አሰራር ለማስቀረት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
እንደ ስምምነቱ መነሻ፣ ሁለቱ ተቋማት በቅርቡ በሚካሄዱ ዓመታዊ የሪል እስቴት ጉባኤዎች እና ቀጣናዊ የኤክስፖ መድረኮች ላይ በጋራ በመሰለፍ የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ ወስነዋል።
ተቋማቱ በጋራ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ትብብሩ በደፈናው የሚመራ ሳይሆን፣ የሁለቱን ወገኖች ኃላፊነት፣ የሥራ ጊዜ ሰሌዳ እና የሚጠበቁ ውጤቶችን በግልጽ በለየ ይፋዊ ስምምነት የሚመራ ነው።
ይህም የዘርፉን ዕድገት በዘፈቀደ ሳይሆን በሳይንሳዊ እና በተጠያቂነት መርህ ለመምራት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።
የሪል እስቴት አልሚዎች ማህበር በዘርፉ ሙያዊ መመዘኛዎች እንዲከበሩና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንዲጠናከር በትኩረት የሚሰራ ሲሆን፣ አጋር ድርጅቱ ዶክሳ ቢዝነስ ትሬዲንግ በበኩሉ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶችን በማሳብ እና የንግድ ትስስሮችን በመፍጠር ረገድ የድርሻውን ይወጣል ተብሏል።
ይህ ስምምነት በተለይም በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ዘርፍ አንገብጋቢ የሆኑትን የመሠረተ ልማት እና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የሀገሪቱን የቤት ልማት እንቅስቃሴ ከአህጉራዊ የንግድ ትስስሮች ጋር ለማቀናጀት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
ኢንዱስትሪው አሁን ካለበት ፈታኝ ሁኔታ ወጥቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ እንዲሆን ለማድረግ ይህ ስምምነት እንደ ትልቅ የማሳያ እርምጃ ተወስዷል።
ልዑል ወልዴ
ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም
