የህጻናት ማቆያ አገልግሎት የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለዉ ተገለፀ

በኢትዮጵያ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እና የህጻናትን ቀደምት እድገት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ፣ የህጻናት ማቆያ አገልግሎትን እንደ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ አድርጎ የመቅረጽ እና የማስፋፋት ስራዎች ተጠናክረው እየተከናወኑ እንደሚገኝም ሰምተናል።

ዘርፉ ለረጅም አመታት ትኩረት ተነፍጎት እና እንደ ቅንጦት ሲታይ የቆየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ከግል ባለሀብቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ የህጻናት ማቆያ ሞዴሎች በተግባር ላይ እየዋሉ መሆናቸው ተመልክቷል።

በጉዳዩ ላይ የማርኬት ሲስተም አማካሪ የሆኑት አቶ ተስፋየሱስ አለማየሁ እንዳብራሩት፣ ቀደም ሲል በዘርፉ በቂ የግንዛቤ እጥረት እንደነበረ እና ህጻናትን ማቆየት እንደ ቅንጦት ይታይ ስለነበር የፖሊሲ አጀንዳ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

ይህም እናቶች ልጆቻቸውን የሚከባከብላቸው በማጣታቸው ምክንያት ከስራ ገበታቸው እንዲቀሩ ወይም ምርታማነታቸው እንዲቀንስ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ እንደቆየ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ በተደረጉ የገበያ ጥናቶች እና የፖሊሲ እንቅስቃሴዎች አዎንታዊ የግንዛቤ ለውጥ መምጣቱ ተጠቅሷል።

አሁን ላይ አገልግሎቱን በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አዳዲስ የመንግስት፣ የግል እና የማህበረሰብ አቀፍ የዴይ-ኬር ሞዴሎች ተቀርጸው ወደ ተግባር እየገቡ ይገኛሉ።

በተጨማሪም የህጻናት ተንከባካቢዎችን (ናኒዎችን) የሙያ ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችል ብሄራዊ የስልጠና ካሪከለም ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተዘጋጅቶ ሲጠናቀቅ፣ በቀጣይ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በኩል በስፋት የሚሰጥ ይሆናል።

ለአለም አሰፋ

ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *