የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 34 ተጠርጣሪዎች እና 14 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ከሀምሌ 16 እስከ ሀምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ባደረገው ክትትል 661 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 43 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የወጭ፣ በድምሩ 704 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዙን አስታውቋል፡፡
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ በአዋሽ ቅርንጫፍ 261 ሚሊዮን ብር ፣ በአዲስ አበባ ኤርፖርት 111 ሚሊዮን ብር እና በጅግጅጋ 90 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን በመያዝ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል፡፡ ኮሚሽኑ ቀሪው ከ242 ሚሊዮን ብር በላይ የተያዙባቸውን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በመረጃው ላይ ይፋ አላደረገም፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አዳዲስ እና ልባሽ ጨርቆች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ እቃዎች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የቁም እንስሳት ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ መድኃኒት፣ ማዕድናት እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በጥቆማ እና በበረራ ነው ተይዘዋል የተባለው፡፡ የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 34 ተጠርጣሪዎች እና 14 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮንትሮባንድን ለመከላከል ለብቻዬ የማደርገው እንቅስቃሴ በቂ አይደለም ያለው ኮሚሽኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አዲስዓለም አበበ
ሐምሌ 24/ 2018 ዓ.ም
