በፍርድ ቤት የተጠየቁ ማስረጃዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ባለመገኘታቸዉ እልባት ያላገኙ መዝገቦች መኖራቸዉን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተናገረ፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጠቅላይ እና በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እልባት ሳያገኙ የቆዩ መዛግብት መኖራቸዉን ተመልክቻለሁ ሲል የበጀት አመቱን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ገልጿል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ አለም አንተአግደዉ እልባት ሳያገኙ በቆዩት መዝገቦች ዙሪያ ጥናት መደረጉን አስረድተዋል።
በዚህም በፍርድ ቤት የተጠየቁ ማስረጃዎች ለማቅረብ የፀጥታ ችግር እንደ እክል መታየቱን ጥናቱ አሳይቷል።
ከነዚህ መካከል በፍርድ ቤት የተጠየቁ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ማስረጃ የሚሰጡ ተቋማት በፀጥታ ችግር ምክንያት ስራ ላይ ባለመሆናቸዉ ተደጋጋሚ ቀጠሮ ለመስጠት ምክንያት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ ማስረጃ የሚሰጡ ተቋማት ጋር የተጠየቀዉን ማስረጃ ሄዶ ለማጣራት በፀጥታ ችግሩ ምክንያት ያን ማድረግ እንዳልተቻለም በጥናቱ መለየቱን ገልፀዋል።
ባለጉዳዮችም ቢሆኑ የፀጥታ ችግሩን ተንተርሶ ተደጋጋሚ ቀጠሮ መጠየቃቸዉ እንዲሁም በወቅቱ ሊሰጡ የሚገቡ ትዕዛዞች በመዘግየታቸዉ መዝገቦቹ እልባት ሳያገኙ እንዲቆዩ እንዳደረጋቸዉ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተናግሯል።
ከዚህ ዉጪ በአንዳንድ ማስረጃ ሰጪ ተቋማት የሚቀረቡ ማስረጃዎች የገለልተኛነት ጥያቄ ሲነሳ ገለልተኛ ነዉ ተብሎ በሚታመንበት ሌላ አካል ማስረጃ እንዲሰጥ ትዕዛዝ መሠጠቱ እንደ ችግር ተነስቷል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አለም አንተአግደዉ በሪፖርታቸዉ የዳኞች ስነምግባርን በተመለከተ እንደገለፁት በ80 ዳኞች ላይ የዲሲፕሊን ክሶች ቀርበዋል ብለዋል።
ከዚህ ዉስጥ 51ዱ ዉሳኔ ያገኙ ሲሆን፤ 36 ያህሉ ጥፋተኛ ሆነዉ በመገኘታቸዉ ከገንዘብ እስከ ስራ ስንብት የደረሰ እርምጃ እንደተወሰደባቸው በሪፖርታቸዉ ገልጸዋል።
ቁምነገር አየለ
ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም
