አረንጓዴ አሻራ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ውጤታማ መሣሪያ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርን አስመልከተው ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት÷ ባለፉት 7 ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸው በመንግሥትና በሕብረተሰቡ መካከል የተጠናከረ ትብብር የተመዘገበበት ታሪካዊ ስኬትና የዘመኑ ትልቅ ሀገራዊ ትሩፋት ነው ብለውታል።
 
አዲስ አበባም ከመርሐ ግብሩ ጅማሬ አንስቶ ከ90 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቷን ከንቲባዋ አስታውሰዋል።
 
ከንቲባዋ አክለው”በ2018 ዓ.ም 6 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅደንም እስካሁን 5 ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆኑትን ተክለናል። በዛሬው የአንድ ጀምበር መርሐ ግብር ደግሞ አንድ ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ። በሁሉም ክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎች፣ ብሎኮች፣ የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም የግል ኩባንያዎች የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።” ብለዋል፡፡
 
 ችግኝ መትከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የአካባቢ ውበትን ለመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። በተለይም በአዲስ አበባ እየጨመረ የመጣውን የጎርፍ ተጋላጭነት ለመቀነስ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትልቅ መፍትሔ መሆኑን አስምረውበታል።
 
ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ÷ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተተከሉትን የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነት የሁሉም ዜጎች የጋራ አደራ መሆኑን በማስገንዘብ፣ የተፈጠረውን አረንጓዴ ሀብት በጋራ በመጠበቅ ዘላቂነቱን እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል።
 
ሐምሌ 27 /2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *