በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ ባሉ መንገድና ህንፃዎች ላይ አሁንም የጥራትና የስታንዳርድ ክፍተቶች በመኖራቸው፣ በአካል ጉዳተኞች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ስጋት መደቀኑ ተገለጸ።
የመሰረታዊ አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ህብረት መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አማሃ ገብረማርያም ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ በከተማዋ ከተደረገ ጥናት ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑ ህንፃዎችና መሰረተ ልማቶች ለአካል ጉዳተኞች አመቺ አይደሉም ብለዋል።
“አብዛኞቹ ራምፖችና ሊፍቶች መስፈርቱን ያላሟሉ በመሆናቸው አካል ጉዳተኞች በትምህርት፣ በጤና እና በማህበራዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ከፍተኛ መሰናክል ገጥሟቸዋል። በተለይ በክረምት ወቅት የሚፈጠሩ የጎርፍ አደጋዎች፣ ያልተሸፈኑ የፍሳሽ መስመሮችና ክፍት ጉድጓዶች አደጋውን ያባብሱታል። ስለዚህ የጥራት ጉድለት ያለባቸው ግንባታዎች እስከ ማስፈረስ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።”ሲሉ ይገልጻሉ አቶ አማሃ፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን በበኩላቸው፤ በተለይ በኮሪደር ልማት ስራዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አሰራሮች መተግበር መጀመራቸውን ገልጸዋል።
አቶ እያሱ ሰለሞን ለጣበያችን እንዳሉት “ለእግረኞችና ለዊልቸር ተጠቃሚዎች የሚሆኑ ሰፋፊ መንገዶችና ራምፖች፣ እንዲሁም ለዐይነ ስውራን የተለዩ የጉዞ መስመሮች እየተዘጋጁ ይገኛሉ። በቀጣይ የአምስት አመት እቅዳችን ውስጥም አካታች የሆኑ ስራዎች ተካተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በክረምት ወቅት ለሚከሰቱ የመንገድ ብልሽቶችና ክፍት የማንሆል ክዳኖች ፈጣን የጥገና ስራዎች እያከናወንን ነው፡፡” ብለዋ፡፡
ሀናን ሸምሱ
ነሐሴ 05/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የስታንዳርድ ክፍተት አለባቸው ተባለ።
