ቢያንስ የ1መቶ11 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን የ7.4 ማግኒቲውድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለመጠለያ፣ ለምግብ እና ለጥበቃ የሚውል በጀት መድቧል።
‹‹በተለያዩ የኮሎምቢያ ክልሎች የተከሰተውን አውዳሚ የ7.4 ማግኒቲውድ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ፣ የትራምፕ አስተዳደር ለአስቸኳይ ጊዜ መጠለያ፣ ምግብ፣ ጥበቃ እና የመሬት መንቀጥቀጥ ጉዳት ዳሰሳ የሚውል 15.5 ሚሊየን ዶላር እየመደበ ነው›› ሲል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው ጽሁፍ አስታዉቋል፡፡
‹‹ከኮሎምቢያ ህዝብ ጋር በጸሎት አብረን ነን፤ እንዲሁም ፕሬዝዳንት አቤላርዶ ዴ ላ ኤስፕሪላ እና መንግስታቸው በስፍራው ያለውን ፍላጎት በሚገመግሙበት ወቅት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን›› ብሏል።
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ መስሪያ ቤቱ በመሬት መንቀጥቀጡ የተጎዱ አሜሪካውያን ዜጎችን እየረዳ መሆኑን ገልጸው፤በኮሎምቢያ የሚገኙ አሜሪካውያን የቆንስላ አገልግሎት እና እርዳታ ለማግኘት በቦጎታ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲያመሩ አሳስበዋል።
የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ጥናት መረጃ እንደሚያመለክተው፥የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ከኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ በስተምዕራብ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የቾኮ ክልል፣ ሳን ሆሴ ዴል ፓልማር አቅራቢያ ሲሆን፥ወደ 107 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ነበረው።
የኮሎምቢያ ባለስልጣናትእንዳስታወቁት፤በአደጋው ቢያንስ 1መቶ11 ሰዎች ሲሞቱ 87 ሰዎች ቆስለዋል።
እንዲሁም ቢያንስ 61 ሙሉ በሙሉ የፈረሱትን ጨምሮ ወደ 1 ሺህ 6መቶ የሚጠጉ ህንጻዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 05/2018 ዓ.ም
