በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፣ በዳውሮ ዞን የታርጫ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ እና የመንገድና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት በጋራ ባደረጉት የተቀናጀ ክትትል፣ ባለፉት 10 ወራት ከሕጋዊ ታሪፍ በላይ ከተሳፋሪዎች የተሰበሰበ 680 ሺህ ብር ማስመለስ ተችሏል።
የከተማ አስተዳደሩ መንገድና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት በአካባቢው የሚሰጠው የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ሕግና ሥርዓትን የተከተለ እንዲሆን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዘነበ ዘለቀ ከደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በበጀት ዓመቱ ከሕዳር ወር ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ከሕጋዊ ታሪፍ በላይ ተጨምሮ ከተሳፋሪዎች የተሰበሰበውን 680 ሺህ ብር በማስመለስ ለተገልጋዩ ማኅበረሰብ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም፣ ከታሪፍ በላይ የማስከፈል ሙከራዎችን እና በሌሊት የሚደረጉ ሕገ-ወጥ ጉዞዎችን ለማስቀረት ከአጎራባች ዞኖች የትራንስፖርት አካላት ጋር በቅንጅት የመሥራት እንቅስቃሴ ተጀምሮ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።
በመጨረሻም፣ የተሳፋሪዎችን መብት ለማስከበርና ጤናማ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስፈን የሕብረተሰቡ ትብብር ከፍተኛ መሆኑን አቶ ዘነበ ጠቁመው፣ ማኅበረሰቡ የሚያደርገውን አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸው ተዘግቧል።
ነሐሴ 07/2018 ዓ.ም
የታርጫ ከተማ አስተዳደር ከታሪፍ በላይ የተወሰደ ከ680 ሺህ ብር በላይ ለተሳፋሪዎች አስመለሰ
