‹‹አዲሱ የካሳ አዋጅ›› ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች ማነቆ እንደሆነበትም ጨምሮ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በልማት ፕሮጀክቶቹ ምክንያት በሚነሱ የካሳ ክፍያዎች ዙሪያ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ከፍተኛ የክርክርና የይገባኛል ጥያቄ እንደገጠመው ዋና ሥራ አስፈጻሚዉ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።
ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት፤ ተቋሙ አዳዲስ የልማትና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ሲያስፋፋ ለሚነሱ ዜጎች የሚከፈለውን የካሳ መጠን በተመለከተ ሰፊ ተግዳሮት ደቅኖበታል።
በአሁኑ ወቅትም ከተለያዩ አካላት ጋር ተያይዞ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ የካሳ ክፍያ ክርክር ያለበት ሁኔታ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ለችግሩ መባባስ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አዲሱ የካሳ ክፍያ አዋጅና የአፈጻጸም መመሪያዎች አለመውጣት ዋና ማነቆ መሆናቸውን ኢንጂነሩ ጠቁመዋል።
አዋጁ ከወጣ በኋላ ዝርዝር መመሪያ ባለመዘጋጀቱ ምክንያት የካሳ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስና ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአንዳንድ ክልሎች በኩል ከእውነታው የራቀና ካላግባብ የሚቀርብ የሀሰት መረጃዎችን መሰረት ያደረገ ከፍተኛ የካሳ ጥያቄ እንደሚቀርብ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህም በተቋሙ የፋይናንስና የአሰራር እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አብራርተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ያሉ ሌሎች ተቋማት ተመሳሳይ የካሳ ችግር ቢያጋጥማቸውም፤የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ግን በአየር ላይ (በአናት ላይ) የሚያልፍ በመሆኑ ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ልዩ ተግዳሮት እንደሚያጋጥመው ተገልጿል።
ኢንጂነር አሸብር አክለውም፤ ተቋሙ የችግሩን አጣዳፊነት በመገንዘብ አስፈላጊውን ግምገማ በማካሄድ ለመንግስትና ለገንዘብ ሚኒስቴር የመፍትሔ ሃሳብ ማቅረቡንና በቅርቡ ዘላቂ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
ለዓለም አሰፋ
ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም
