በኔፓል ትሪሹሊ ወንዝ ዳርቻ በተቆፈሩ እና በጭቃ በተሞሉ ረጅም ዋሻዎች ውስጥ ተቀርቅረዋል ተብለው የሚገመቱ ከ600 በላይ ሠራተኞች፤ ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በሕይወት ይገኛሉ የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የተረፉ ሰዎችን ለማዳን ያለው ወሳኝ ጊዜ እያለቀ ነው ከሚል ስጋት በመነሳት ወደ ትሪሹሊ-3ኤ ፕሮጀክት ቦታ አዉሮፕላን ለማስገባትና መንገድ ለመክፈት ኮረብታውን በፈንጂ በማፈንዳት የሕይወት አድን ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
በኔፓል እና ቲቤት ድንበር ላይ በደረሰው የጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 9መቶ39 መድረሱን የሀገሪቱ የአደጋ ስጋት አመራር ባለስልጣን አስታውቋል።
መሥሪያ ቤቱ የጠፉ ሰዎች ቁጥር 3ሺ9መቶ25 መድረሱን የገለጸ ሲሆን፤ከነዚህም መካከል 5መቶ92 ያህሉ የውጭ ሀገር ዜጎች እንደሆኑ አሳውቋል።
የኔፓል ጠቅላይ ሚኒስትር ባሌንድራ ሻህ እንደተናገሩት፤ በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫዎች ውስጥ ይሠሩ ከነበሩ ሠራተኞች መካከል 2 መቶ79 ሰዎች መዳናቸውን ገልጸዋል።
የማዳን ሥራው በቻይና እና ኔፓል ወታደራዊ አባላት በተቋቋመ ዓለም አቀፍ ቡድን እየተመራ የሚገኝ ሲሆን፤በተጨማሪም የሕንድ፣ የኮሪያ እና የአውስትራሊያ ባለሙያዎች በሥራው ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ነገር ግን ከነፍስ አድን ሰራተኞች መካከል አንድ ቡድን ሰኞ ዕለት ማለዳ ወደ አንዱ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ በሚወስደው ዋሻ ውስጥ መግባት የቻለ ቢሆንም ምንም ሰው ሳያገኝ ተመልሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ የሕይወት አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዉ፤ በሀገሪቱ ጎርፉ ‹‹የተለመደ›› ክስተት አለመሆኑንም ጠቁመው፤ ይህ አጋጣሚ በሂማላያ ክልል ውስጥ የሚገጥሙን አደጋዎች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ እየጨመሩ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል።
ሀና ሰይፉ
ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም
