ሰራተኞችን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ እንጂ ችግር ፈጣሪ አልያም ተቃዋሚ አድርጎ መመልከት አይገባም ያለዉ ኮንፌዴሬሽኑ፥ሰራተኞች በመደራጀታቸዉ እና ጥያቄ በማንሳታቸዉ የማህበር መሪዎች እየታሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ከ3 መቶ በላይ ህጋዊ እዉቅና ያላቸዉ የሰራተኛ ማህበራት እንዲደራጁ ተደርጓል ሲል የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ተናግሯል።
ኮንፌዴሬሽኑ በተጠናቀቀው የበጀት አመት 4መቶ 28 መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበራት መደራጀታቸውን አስታዉቋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ( ኢሰማኮ) የማህበር መሪዎች ያለ አግባብ የቦታ ዝዉዉር እርምጃ እና ሰራተኞች በመደራጀታቸዉ እስር እየገጠማቸው እንደሚገኝ ተናግሯል።
የኮንፌዴሬሽኑ ኘሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፥እስከ ሰኔ 30 ድረስ ባለዉ ጊዜ 4መቶ 28 የሰራተኞች ማህበራት መደራጀታቸዉን ገልፀዉ፤3መቶ 45ቱ ህጋዊ እዉቅና ያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሰራተኞች ማህበራት እና በድርጅቶች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በድርድር መፍትሄ እንዲያገኙ፤ መፍትሄ ማግኘት ያልቻሉትን ደግሞ በፍርድ ቤት መፍትሔ እንዲገኝላቸዉ የህግ ድጋፍ እየተሰጠ ይገኛል ተብሏል።
የማህበራት መደራጀትን እንደ ተቃዋሚ መመልከት አይገባም የሚሉት የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት፥ ሰራተኞች ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ አጋዥ እንጂ ችግር ፈጣሪ ሆነው መታየት የለባቸውም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እንዲወስን የሚያስችለው ቦርድ እንዲቋቋም ደንብ ቢዘጋጅም እስካሁን መፅደቅ አለመቻሉን ገልጿል።
በወር 1 ሺህ እና 2 ሺህ ብር ተከፍሎት የሚሰራ ሰራተኛ እየኖረ ነዉ ወይ? የሚሉት የኮንፌዴሬሽኑ ኘሬዝዳንት አቶ ካሳሁን፥ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል መወሰኑ ግዴታ መሆኑን እና ይህን ለማድረግ ግን ችግሮች እንደበዙ ተናግረዋል።
ቁምነገር አየለ
ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም
ሰራተኞች ማህበራትን ማደራጀታቸው እንደ ተቃዉሞ እና ችግር ፈጣሪ ተደርጎ መታየት የለበትም ሲል ኢሰማኮ ተናገረ
