በኬንያ የሚኖሩ ቡሩንዲያውያን በስጋት ሀገሪቱን ለቀው እየወጡ መሆኑ ተሰማ

በኬንያ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚሰሩባቸው አነስተኛ የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቡሩንዲያውያን በስጋት ሀገሪቱን ለቀው እየወጡ መሆኑ ተዘግቧል።

የቡሩንዲ መንግስት ድርጊቱን በፅኑ ሲያወግዝ፣ የኬንያ መንግስት በበኩሉ የፕሬዝዳንቱ ንግግር “በተሳሳተ መልኩ ተተርጉሟል” በሚል ይቅርታ ጠይቋል።

ባለፈው ሳምንት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚሰሩባቸው አነስተኛ የንግድ ስራዎችና የጎዳና ላይ ንግዶች እስከ ሰኞ ድረስ እንዲዘጉ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው “ኬንያ ለጎዳና ላይ  ነጋዴዎች  ተብሎ የተገነባ የኢንቨስትመንት መዋቅር የላትም” ማለታቸውን ተከትሎ፣ በናይሮቢና አካባቢው በሚኖሩ የውጭ ዜጎች በተለይም በቡሩንዲያውያን ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቡሩንዲያውያን በናይሮቢ የሚገኘውን የሀገራቸውን ኤምባሲ በመክበብ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚያስችሏቸውን የጉዞ ሰነዶች ለማግኘት ሲጋፉ መዋላቸው ተዘግቧል።

በስፍራው የነበሩ የሃይማኖት አባት ፓስተር ዣን ባፕቲስት ለኤኤፍፒ (AFP) በሰጡት ቃል “እንደ እንስሳ ነው ያባረሩን” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ፓስተሩ አክለውም ጎረቤቶቻቸው ጥቃትና ዘረፋ እንደደረሰባቸው በመጥቀስ፣ ሁኔታውን በደቡብ አፍሪካ ከሚስተዋለው የውጭ ዜጎች ጥላቻ (Xenophobia) ጋር አነጻጽረውታል።

የቡሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤድዋርድ ቢዚማና በበኩላቸው በዜጎቻቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በፅኑ አውግዘዋል።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ “ሲቪሎች የፖሊስን ስራ እንዲሰሩ መፍቀድ ሀገሪቱ መፍረሷን የሚያሳይ ነው” ካሉ በኋላ፣ የኬንያ መንግስት ለዜጎቻቸው ደህንነት ተጠያቂ መሆኑን አሳስበዋል።

ይህንን ተከትሎ የኬንያው የውጭ ጉዳይ  ሚኒስትር ድኤታ ኮሪር ሲንግ ኦኢ በቡሩንዲ ኤምባሲ በመገኘት ይቅርታ ጠይቀዋል።

ሚኒስትሩ የፕሬዝዳንት ሩቶ ንግግር “በተሳሳተ መንገድ መተረጎሙን” ገልጸው፣ የመንግስታቸው ዋና አላማ ነዋሪዎች ህጋዊ መታወቂያ እንዲኖራቸውና ስራቸውም እንዲመዘገብ ለማድረግ እንጂ ዜጎችን ለማባረር እንዳልሆነ አስረድተዋል።

የኬንያ መንግስት ቃል አቀባይ ቻርለስ ኦዊኖ በበኩላቸው፣ በርካታ የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች ያለ ሙሉ ሰነድ በኬንያ እንደሚኖሩ በመጥቀስ፣ አሁን ላይ ሰነዶቻቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያስችል የሁለት ሳምንት የዲጂታል ምዝገባ እድል መከፈቱን አስታውቀዋል።

ምንም እንኳን የኬንያ መንግስት ማብራሪያና ይቅርታ ቢጠይቅም ፣ አሁንም ድረስ በርካታ ቡሩንዲያውያን በስጋት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገልጿል።

ልዑል ወልዴ

ጳጉሜ 3/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *