በመንግስት በኩል በተከናወነ ጥናትና ከክልሎች በተሰበሰበ ትክክለኛ መረጃ መሰረት፣ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ቁጥር 2.9 ሚሊዮን ብቻ ነው ያለው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ነው።
ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የተረጂዎችን ቁጥር እያጋነኑ ይገልጻሉ ሲሉ የገለጹት የኮሚሽኑ የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሻግሬ ተሾመ፤ ድርጅቶቹ ለራሳቸው የፕሮጀክትና የሰራተኛ ደመወዝ በጀት ማሟያ ሲሉ መረጃዎችን እንደሚያዛቡ ነው ያስረዱት።
አቶ አሻግሬ ተሾመ ይህንን ያሉት በአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አዘጋጅነት በኤል-ኒኖ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለፌደራልና ለክልል የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በመድረኩ በሰጡት ማብራሪያ “በስማችን የሚነገደው የዕርዳታ ንግድ መቆም አለበት” ያሉት አቶ አሻግሬ፤ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በአካል ጉዳት፣ በእርጅና፣ በመፈናቀል፣ በከተማና ገጠር ሴፍቲኔት እንዲሁም ከስደት ተመላሾች በሆኑ ስድስት የህብረተሰብ ክፍሎች የተለዩና በድምሩ 2.9 ሚሊዮን የሆኑ ዜጎች ናቸው በማለት ተናግረዋል።
አዲስዓለም አበበ
መስከረም 20/2019 ዓ.ም
