ዶናልድ ትራምፕ የወባ መድሀኒትን ኮሮናን እንዲከላከልላቸው እየወሰዱት መሆኑን ተናገሩ፡፡

ሀይድሮክሲ ክሎሮክዊን የተባለው የጸረ ወባ መድሀኒት በጤና ባለሙያዎችና በአሜሪካ የምግብና የመድሀኒት አስተዳደር ውጤታማነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ብቻ ሳይሆን የጎንዮሽ ጉዳትም ስላለው እንዳይወሰድ ማሳሰቢያ ተሰጥቶበታል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ከባለሙያዎቹ በተቃራኒ የፀረ ወባ መድሀኒት ኮሮናን ያድናል ብለው ካመኑ ቆየት ብለዋል፡፡

የነጩ ቤተ መንግስት ዶክተርን አማክሬ የፀረ ወባ መድሀኒትን ወስጃለሁ ሲሉ ትናንት ተናግረዋል፡፡

ዶክተሩ መድሀኒቱ እንዲወሰድ መክሯል ከማለት ተቆጥበዋል፡፡

በኋላ ለአንድ ሳምንት ከግምሽ ነው የወሰድኩት ብለው የወሰዱበትን የቀን ብዛት ቢያርሙም ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ በየቀኑ ነው የፀረ ወባ መድሀኒቱን ስወስድ የከመርኩት ብለው ነበር ትራምፕ፡፡

ትራምፕ በአሜሪካ ኮሮና ከገባ ሰሞን ጀምሮ ጸረ ማሌሪያ መድሀኒቱ ኮሮናን እንደሚያድንና የኮሮና ታማሚዎች ቢሞክሩት የሚያጡት ጥቂት ነው እያሉ ሲወተውቱ ነበር፡፡

ከጤና ባለሙያዎች ግን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡

አንድ ጥናት ደግሞ ኮቪድ 19 ን አያድንም ከማለቱ በተጨማሪ የልብ ህመም ችግር ሊያስከትል መቻሉን አረጋግጫለሁ ብሎ ነበር፡፡

በአሜሪካ የህክምና ማህበር ጆርናል ላይ የታተመ ሌላ ጥናት ደግሞ ሀይድሮክሲ ክሎሮክዊን ኮሮናን አያድንም ብሏል፡፡

በኒው ኢንግላንድ የህክምና ጆርናል ላይ የታተመ ሌላም ጥናት እንዲሁ የፀረ ወባ መድሀኒት ኮሮናን የማጥፋት አቅም የለውም ሲል አትቷል፡፡

ስለ ጸረ ወባ መድሀኒት ማስረጃዬ ግንባር ቀደም ሆነው ቫይረሱን እየተዋጉ ካሉ የጤና ባለሙያዎች ያኘሁት አዎንታዊ አስተያየቶች ናቸው ሲሉ ትራምፕ በእርግጠኝነት መንፈስ ተናግረዋል፡፡

የነጩ ቤተ መንግስት ዶክተርን ምን ታስባለህ ብዬ ጠየኩት፤ ከፈለክ ውሰድ አለኝ ብለዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎች የፀረ ወባ መድሀኒት ሀይድሮሎክሲ ክሎሮክዊን እና ክሎሮክዊን ለኮሮና ቫይረስ ህክምና እንዳይወሰዱ በጣም እያስጠነቀቁ ነው፡፡

ጥቅም ላይ እንኳን መዋል ያለባቸው ሆስፒታል ውስጥና ለላብራቶሪ ምርመራ ነው፣ ምክንያቱም ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት፤ እስከመግደል ሊያስከትሉ ስለሚችሉ እያሉ ነው፡፡

ነገሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ ትራምፕ በእሳቸው እድሜ ሊያጋጥም የሚችለው የልብ ህመም ችግር ያለባቸው ሲሆን የአኗኗር ዘዬ ለውጥ ካላመጡና የሚወስዱትን የኮሌስትሮል መጠን ካልቀነሱ ከሶስት እስከ አምስት አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ከባድ የልብ ድካም ይገጥማቸዋል መባሉን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል ።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *