የሚዲያ ባለሙያዎች የኮድ ሁለት ተራ አይመለከታችሁም ብንባልም ፍቃድ እያገኘን አይደለም አሉ።

በወጣው የሙሉ እና ጎዶላ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥር ስምሪት መመርያ ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች እየቀረቡ ሲሆን ለሙስና ተጋላጭነቱ በስፋት እየተነሳ ነው፡፡

በመመርያው የሚዲያና ጤና ተቋም ባለሙያዎች ልዩ ፈቃድ ስላገኙ ሙሉና ጎዶሎ ተራ ውስጥ አልገቡም፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎች ለኢትዮ አፍ ኤም እንደተናገሩት ሁኔታው የኮሮና ቫይረስ የፈጠረውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመግታት የሚያግዘውን ስራቸውን እንኳን እንዳይከውኑ እንቅፋት እንደፈጠረባቸው ነው፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎች ለጣቢያችን እንደተናገሩት ሲጀመር የኮድ 2 መኪናዎችን በተራ እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ አስፈላጊነት አልታየንም ብለዋል፡፡

የቤት መኪናውን የማይጠቀመው ሰው ትራንስፖርቱን ማጨናነቁ የማይቀር ሲሆን ራይድ ቢጠቀምም የራሱን መኪና ይዞ ቢወጣም መንገድ ላይ የሚፈጥረው መጨናነቅ ተመሳሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስራችን ላይ እክል እየፈጠረብን ነው የሚሉት ጋዜጠኞቹ ለጤናና ለሚዲያ ባለሙያዎች የይለፍ ፍቃድ ወስደው ካለተራ ኮድ ሁለት መኪናቸውን መጠቀም ይችላሉ በተባለው መሰረት ፍቃድ ልንጠይቅ ስንሄድ በአካል አይቻልም በኢንተርኔት በተዘጋጀው ማመልካቻ መሰረት አመልክታችሁ ፍቃዱን ማግኘት ትችላላቹ ተባልን ብለዋል፡፡

በኦንላይን የመስሪያ ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ፣ሊብሬ፣መታወቂያ ከማመልከቻችሁ ጋር አያይዙ በተባልነው መሰረት አያይዘን ብንልክም ከ10 ቀን በላይ አልፎናል እስካሁን ግን የተሰጠን ፍቃድ የለም ሲሉ ተናግዋል፡፡

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ለዚህ ብሎ ባዘጋጀው ድረ ገፅ ላይ ያለው ስልክ ቁጥር ካለመስራቱም በላይ ፤ ካመለከትን በኋላ በነጋታው ማመልከቻችን ያለበትን ደረጃ ስናይ የሌላ ሰው ሊብሬ፣መታወቂያና የድጋፍ ደብዳቤ እናገኛለን ፤ በትክክል የሚሰራም አይመስለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌሎች ደግሞ ግልጽ ባልሆነ መንገድ በአቋራጭ ፍቃድ የሚያገኙ እንዳሉ እናያለን እንዴት እንደሆነ አልገባንም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ እስከ ሚያዚያ 25 ድረስ መመርያውን ባላከበሩ 1 ሺህ 351 አሸከርካሪዎች ላይ ቅጣት ተጥሏል ብለዋል፡፡

በመቅጣት ሂደቱ ላይ ታራፊኮች ለሙስና ሊጋለጡ እንደሚችሉ የሚነሳውን ሀሳብ እንደሚስማሙበት ገልፀዋል፡፡

5 ሺህ ብር ፣ መንጃ ፍቃድ መንጠቅ በወንጀል እስከ መጠየቅ የሚለው አሰራር ለሙስና መንገድ እንደሚከፍት ግልፅ ቢሆንም የቁጥጥርና የቅኝት ስራዎችን እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ከዚያ በዘለለ ትራፊኩ ላይ እምነት መጣል ነው የምንችለው ያሉ ሲሆን ህብረተሰቡም መሰል ወንጀሎችን ሲያይ ቢጠቁመን በሙስናው የተሳተፉትን አካላት እንዲቀጡ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም ብለዋል፡፡

ባለፉት 15 ቀናት መመርያ የመተላለፉ ችግር ቀንሶ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ አረጋዊ ፍቃድ አሰጣጥን የተመለከቱት በሚዲያ ባለሙያዎችና በበጎ ፍቃደኞች የሚነሳው ቅሬታ ወደ ፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ነው መሄድ ያለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወደ ፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልኩ አይነሳም።

በአካል ወደ ተባለሰልጣኑ ስንሄድም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሰው መግባት አይችልም የሚል ምላሽ በመስጠት ከበር መልሰውናል።

ይመለከተዋል ወደ ተባለው የስራ ሃላፊ ስንደውል ደግሞ የሚመለከተው እሷን ነው በማለት ወደ ሌላዋ ሲልከን እሷ ደግሞ ራሱኑ ነው የሚመለከተው በሚል ከአንዱ የስራ ሀላፊ ወደ ሌላው የስራ ሀላፊ ስንዘዋወር የተፈለገውን መረጃ ሊሰጡን አልተቻልንም፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ። https://t.me/ethiofm107dot8

በሔኖክ አስራት
ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *