የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ የቆጣሪ ማንበቢያ ዘመናዊ መሳሪያ በስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ።

ተቋሙ ከቆጣሪ ንባብ ጋር በተያያዘ የሚስተዋልበትን የአሠራር ክፍተት ለመፍታት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቆጣሪ ማንበቢያ መሣሪያ ስራ ላይ አውሏል፡፡

ተቋሙ በስራ ላይ ያዋለው የቆጣሪ ማንበቢያ መሳሪያ ኮመን ሜትር ሪዲንግ ኢንስትሩመንት /CMRI/ የተሰኘ በእጅ የሚያዝ ዘመናዊ መሳሪያ ሲሆን፤ የቆጣሪ አንባቢ በእያንዳንዱ የድህረ ክፍያ የቆጣሪ ተጠቃሚ ደንበኛ አካባቢ ሄዶ እንዲያነብ የሚያስገድድ ነው፡፡

ይህም ከኤሌክትሪክ የፍጆታ ሂሳብ ንባብ ጋር በተያያዘ የሚቀርቡትን ቅሬታዎች ለመቀነስ የሚያስችል ነው፡፡

መሳሪያው ሙሉ በሙሉ በስራ ላይ የዋለው በሙከራ ደረጃ በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በስራ ላይ ውሎ አዋጭቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡

በስራ ላይ የዋለው ቆጣሪ ማንበብ መሳሪያ በ50 ሜትር ወይም ከዚያ ባነሰ ርቀት ላይ በመሆን የደንበኛ ተከታታይ ቁጥር በማስገባት የቆጣሪ ንባብ መውሰድ የሚስችል ሲሆን፤ የተቀዳውን ንባብ ትክክለኛ መሆኑንና አለመሆኑን ለማረጋገጥም ለአንባቢው እድል የሚሰጥ ነው፡፡

መሳሪያውን በስራ ላይ ማዋል ያስፈለገው ከዚህ በፊት የነበረው የንባብ አወሳሰድ ዘዴ ኋላቀርና በወረቀት የሚሰራ በመሆኑ ለስህተት የተጋለጠ፣ የተነበበውን ንባብ ወደ ሲስተሙ ለማስገባት የሚወስደውን ጊዜ ስለሚያሳጥር ነው፡፡

መሳሪያው የንባብ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የአሰራር ሂደቶችን ለማፋጠን፣ የጊዜና የሃብት አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ በወረቀት ላይ የተመሰረተ አሰራር ስርዓትን ለማስቀረት፣ የንባብ ምዝገባ ስህተቶችን ለማስወገድ፣ የደንበኞ ቅሬታን ለመቀነስ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደንበኞች ሂሳባቸውን በወቅቱ እንዲከፈሉ እና ተቋሙ ገቢን በብቃት ለመሰብሰብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው፡፡

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት 2 ሺህ በእጅ የሚያዙ የቆጣሪ ማንበቢያ መሳሪዎችን ከ400 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ገዝቶ በከተማ አስተዳድሮችና በክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቢሮዎች በማሰራጨት የንባብ አሠራር ሂደቱን ከወረቀት ስራ ወደ ዲጂታል አሰራር እየቀየረ ይገኛል፡፡ አስከ ታህሳስ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ በሁሉም ማዕከላት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

ተቋሙ ተግባራዊ ያደረገው ዲጅታል የቆጣሪ ማንበቢያ መሳሪያ ፍፁም ግልፅነት ያለውና የአሠራር ሂደትን የሚያሻሽል በመሆኑ ደንበኞች ለተተገበረው የማንበቢያ መሳሪያ ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋጾ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በተጨማሪ ደንበኞች የተቋሙ ቆጣሪ አንባቢ ባለሞያዎች በመኖሪያ ቤቶቻቸው/ድርጅቶቻቸው እየመጡ የማያነቡ ከሆነ በአካባቢው በሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመገኘት ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በሥራ ላይ የዋለው የንባብ መሳሪያው ተቋሙ በቅርቡ ተግባራዊ ካደረገው የኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ካሉት ፓኬጆች መካከል አንዱ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ550 በላይ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ያሉት ሲሆን፤ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞችም አሉት፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያውያን
ሕዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *