የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ አባሉቼ እየታሰሩብኝ ነው አለ።

በቅርቡ የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ታስረዋል መባሉንም አስተባብሏል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጲያ ምርጫ ቦርድ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ተቀዳሚ ሊቀመንበርነት ሲመራ የነበረው ግንባር ለሁለት መከፈል ጋር ተያይዞ አንዱ በሌላው ላይ ጥሎት የነበረውን እግድ አግባብነት የለውም በሚል ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ቦርዱ አደረኩት ባለው ማጣራትም የደረስኩበት ድምዳሜ የፓርቲው ሊቀመንበርም ሆነ በሊቀመንበሩ ታግደዋል የተባሉት ስራ አስፈጻሚዎች ህጋዊ የድርጅቱ አካላት ሆነው ይቀጥላሉ ሲል ውሳኔውን አስተላልፎ ነበር።

እኛም ይህንን ነገር ሰምተናል ግን እስካሁን ከዛኛው ወገን ጋር አልተገናኘንም የሚሉት የኦነግ ቃላ አቀባይ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ምርጫ ቦርድ ቀኑን እና ሰአቱን ሲነግረን የመጀመሪያው ስብሰባ በምርጫ ቦርድ መሰብሰቢያ አዳራሽ የምናደርግ ይሆናል ሲሉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይህንን በተመለከተ ደብዳቤ እንዲፅፍልን ነግረናል ፣ይህም ለጠቅላላ ጉባኤ የመጀመሪያ ዝግጅት እንደሚሆናቸው ቃል አቀባዩ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ዳውድ ኢብሳ ታስረዋል የሚለው ዜናም ሆን ተብሉ ትኩረት ለመሳብ የተነገረ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ ቀጀላ
ከዚህ በፊትም ሊቀመንበሩን በቤታቸው ውስጥ ለእስር ተዳርገዋል በሚል እኛ ጥፋተኛ እንደሆንን በስፋት የስም ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብን ነበር ሲሉም ይናገራሉ ፡፡

ይህ አይነት የስም ማጥፋት ዘመቻ ደግሞ በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ የተለመደ በመሆኑ እኛን ቢያበረታን እንጂ አያስበረግገንም ብለዋል፡፡

የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል በርካታ ከተሞች የሚገኙ አመራሮች እና አባላቶቼ በህግ ማስከበር ስም እንደታሰሩበት ገልጿል።

ይሁን እንጂ መንግስት በህግ ማስከበር ስም ሰበብ ከየትኛውም ወገን ቢሆን ተጨባጭ ባልሆኑ ጉዳዮች የሚያደርገውን የእስር ዘመቻ እንዲያቆም እንጠይቃለን ፤ጥፋተኞች ካሉም በአፋጣኝ ወደ ህግ ቀርበው ወሳኔ ሊያገኙ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ታዬ ደንደዓ የኦነግ ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑን እና እስሩ ፖለቲካዊ አመለካከትን መነሻ ያደረገ ሳይሆን በወንጀሎች ተጠርጥረው መታሰራቸውን ለቪኦኤ መናገራቸው ይታወሳል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ታህሳስ 14 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *