መንግስት ለጣና ሃይቅ የገባዉን ቃል በተገቢዉ መንገድ እየፈፀመ አይደለም ተባለ።

በጣና ሃይቅ ላይ የተጋረጠዉን የእንቦች አረም ለማስወገድ በሚደረገዉ ጥረት የፌደራሉ መንግስት ተገቢዉን ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑ ተነግሯል፡፡

የጣና ሃይቅና ሌሎች የዉሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ አረሙን በማስወገዱ ሂደት ላይም የፌደራሉ መንግስት ቃል ከመግባት ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ እንዲኖረዉ በተገቢዉ መንገድ እየሰራ አይደለም ብሏል፡፡

በኤጀንሲዉ የብዝሓ ህይዎት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ መዝገቡ ዳኘዉ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ብዙን ጊዜ በፌደራሉም ሆነ በክልሉ መንግስት አረሙን ለማስወገድ ቃል ቢገቡም አሁንም ድረስ ግን ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አልቻሉም ነዉ ያሉት፡፡

በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ በጣና ሃይቅ ላይ የተጀመረዉ እንቦጭን የማስወገድ እንቅስቃሴ ጊዚያዊ መፍትሄ ቢያመጣም በዘላቂነት ግን አሁንም ድረስ እንቦጭን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የመጣ መፍትሄ የለም ብለዋል፡፡

የእንቦጭ አረም በጣና ሃይቅ ዙሪያ በ30 ቀበሌዎች እንደተከሰተ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ይህም ከ4 ሺ ሄክታር በላይ የሚሆነዉን የሃይቁን ከፍል አዳርሶታል፡፡በአገር አቀፍ ደረጃ ጣናን እንታደግ በሚል ከሁለት ወር በፊት የተጀመረዉ በሰዉ ሃይል የሚሰረዉ እንቦጭን የማስወገድ እንቅስቃሴ ጊዚያዊ መፍትሄ ማምጣቱም ተነግሯል፡፡

በዚህም አረሙ ከሚገንባቸዉ 30 ቀበሌዎች ዉስጥ በ 24ቱ ቀበሌዎች ወይንም 80 በመቶ የሚሆነዉ እንቦጭ አረም የተወገደ ቢሆንም አሁንም ግን የጣና ሃይቅ ዘላቂ መፍት ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡የፌደራሉም ሆነ የክልሉ መንግስት ቃል ከመግባት ባሻገር በጣና ሃይቅ ዙሪያ ሰፊ የተፋሰሰ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥተዉ እንዲሰሩ አቶ መዝገቡ ጠይቀዋል፡፡

ከጣና ተፋሰሶች የሚነሳዉ ደለል ለእንቦጭ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋዕፅኦ እንዳለዉ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በርብ፤ በመገጭ እና በጉመራ ተፋሰሶች ላይ አፋጣኝ የተፋሰስ ልማቶች ሊሰሩ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡የጣናን ህልዉና ለማስጠበቅ የሚያስችል የአምስት አመት የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ በቅርቡ ወደ ስራ ለማስገባት መታቀዱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ለዚህም መንግስት አስፈላጊዉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

የእንቦጭ አረም ከጣና ሃይቅ በተጨማሪ በአባይ ወንዝ ላይ መታየቱም በህዳሴዉ ግድብ ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

በአባቱ መረቀ
ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *