ብሔር ተኮር የሆኑት የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣዩ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ አጣብቂኝ ውስጥ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
በኦሮሞ ህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳላቸው የሚናገሩት እና በፖለቲካው ተቀባይነት ያላቸው ሰዎችን እንደያዙ የሚነገርላቸው ኦነግና ኦፌኮ በ6 ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ መሳተፋቸውንና አለመሳተፋቸውን እስካሁን እንዳልወሰኑም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ሁለቱ ፖርቲዎች የምርጫ ትብብር ስምምነት ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡
ከቀድሞ ሊቀመንበሩ ጋር ተያይዞ ለሁለት የተከፈለው ኦነግ በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ አከባቢዎች ተንቀሳቅሶ የዕጩዎች ምልመላ እና ፅህፈት ቤቶችን መክፈት ላይ ከፍተኛ ችግር እየገጠመው መሆኑን ለኤትዮ ኤፍ ኤም ተናግሯል፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሳ የቀድሞ ሊቀመንበሩ በምርጫ ቦርድ ከተሰጠው ውሳኔ ውስጥ በቦታቸው ይቀጥሉ የሚለውን ብቻ በመቀበል ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን በተግባር እያሳዩ ነው ይላሉ የፖርቲው ቃል አቀባዩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ፡፡
አቶ ዳውድ ለሽምግልናም አልመች ብለውናል የሚሉት አቶ ቀጀላ በአስቸኳይ ይህ ችግር ቢፈታልን ሌላው ቀላል ነው ይላሉ፡፡
ደጋፊዎቻችን በእጅጉ ግራ ተጋብተዋል ይህ ደግሞ በምርጫው ላይ አስፈላጊውን ድምጽ ለማግኘት ከባድ ሊያደርግብን ይችላል ነው የሚሉት፡፡
ነገር ግን እንዲያም ቢሆን በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ ነገሮችን መቋጨት ቀዳሚ ተግባራችን ነው ብለውናል ፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን እንደ ፓርቲ ተስፋ ሰንቀን በተለይ አራት ፖርቲዎች ሆነን‹‹ ትብብር ለህብር ብሔር ፌደራሊዝም ›› የሚል ጥምርት መስረተናል ሲሉ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ያነሳሉ፡፡
ከኦፌኮ ጋርም ቢሆን በጋራ ለመስራት የትብብር ስምምነት ሰነድ ፈርመናል ብለዋል፡፡
መንግስት የጠየቅነውን መሰረታዊ ነገሮች ካልፈታ በምርጫው መሳተፉ ለውጥ የለውም የሚሉት የኦፌኮ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከኦነግ ጋር የገባነው ስምምነትም ተፈጻሚ የሚሆነው በምርጫው መሳተፋችን ሲረጋገጥ ብቻ ነው ብለውናል፡፡
በያይኔአበባ ሻምበል
ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም
ኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮጵያዊያን
