የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ጊዜያዊ የመንጃ ፈቃድ እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።

ከሰሞኑ አሽከርካሪዎች እየተሰጠን ያለዉ የመንጃ ፈቃድ ጥራት የሌለዉ የወረቀት መንጃ ፈቃድ ነዉ፤ይህ ለምን ሆነ የሚል ጥያቄዎችን በማንሳት ላይ ናቸው።

ለጥያቄያችንም ይሄን ዉሰዱና በኋላ ይቀየርላችኋል የሚል መልስ ይሰጠናል ሲሉ ሾፌሮች ቅሬታቸዉን ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ጣቢያችን በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮን ጠይቋል፡፡

የቢሮዉ የኮምዩንኬሽን ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ እንደነገሩን፤ የአሽከርካሪዎች ቅሬታ እዉነት ነዉ፤አሁን እየሰጠን ያለነዉ የወረቀት መንጃ ፈቃድ ነዉ፤ ይህ የሆነዉ ደግሞ የማሸጊያ ወይም ላሚኔሽን ወረቀት እጥረት በማጋጠሙ ነዉ ብለዉናል፡፡

አቶ አረጋዊ ምክንያቱን ሲያስረዱም፤ በኮቪድ 19 ወቅት ለተወሰነ ጊዜ የመንጃ ፍቃድ የሚሰጡ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ አልነበረም፤በዚያ ወቅት መሰራት የነበረባቸዉ አዳዲስ መንጃ ፈቃዶችና እድሳት የሚያስፈልጋቸዉ መንጃ ፈቃዶች ተጠራቅመዋል፤ አሁን እነዚህን ዉዝፍ ስራዎች ለማጠናቀቅ እየሰራን እንገኛለን፤እጥረቱም ያጋጠመዉ በዚህ ምክንያት ነዉ ብለዉናል፡፡

ታዲያ ችግሩ እስከመቼ ይፈታል ስንል ላነሳንላቸዉ ጥያቄም ከ 3 እስከ 5 ወራት ሊወስድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ዉዝፍ ስራዎችን ካጠናቀቅን በኋላ ወደ መደበኛ ስራችን እንመለሳለን፤በዛን ጊዜ አሁን ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ሁሉ ምላሽ ያገኛሉ ብለዉናል፡፡

አሽከርካሪዎች በበኩላቸዉ እየተሰጠን ያለዉ መንጃ ፈቃድ በቀላሉ ሊቀደድ የሚችልና በእጅ ላብ ሊበላሽ የሚችል በመሆኑ በቶሎ መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በሙሉቀን አሰፋ
የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *