ኢትዮጵያን በአሁኑ ሰዓት የበረሃ አንበጣ መንጋ እንደማያሰጋት ተገለፀ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ለ ኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀው፣ በአሁኑ ሰዓት በሱማሌ ክልል ሲቲ ዞን አካባቢ ላይ አልፎ አልፎ ከሚስተዋለው የአንበጣ መንጋ ውጪ በሌሎች አካባቢዎች ላይ የበረሃ አንበጣ መንጋው አልታየም፡፡

የሚኒስቴሩ የእጽዋት ጥበቃ ዳሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት፣ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ የአንበጣ መንጋው ከሃገሪቱ ጠፍቷል ባይባልም፣ በአሁኑ ሰዓት መንጋው ያለበት ሁኔታ የሚያሰጋ አይደለም ነዉ ያሉት፡፡

ከዚህ ቀደም በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተከሰተውን ይህንን የበረሃ አንበጣ ለመከላከል የሚያስችል የአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ መንጋውን ማጥፊያ መከላከያ መንገዶች ሲሰሩ መቆየታቸውንም ነግረውናል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ የነበረው ይህ የበረሃ አንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ አይዘነጋም።

የዝናብ ሁኔታ ምቹ በሚሆኑባቸው አካባቢዎች ላይ መንጋው የመራባት እድል እንዳለውና ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ያለው የአየር ፀባይ ለመንጋው ምቹ ባለመሆኑ ወቅቱ በራሱ የመከላከል ስራው ማገዙን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና አሁንም አልፎ አልፎ የሚታየው ይህ መንጋ በአስጊ ሁኔታ እንዳይራባ የመከላከሉ ስራ እንደሚሰራ ኢትዮ ኤፍ ኤም ከግብርና ሚኒስቴር ሰምቷል።

በቀይ ባሕር ዳርቻዎች እንደተፈለፈለ የሚገመተዉ የአንበጣ መንጋ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የግብርና ምርት ከ3.5 ሚልዮን ኩንታል በላይ የሚሆነውን ማውደሙን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመለክታል፡፡

በየዉልሰዉ ገዝሙ
መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *