በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ባላቸው የፖለቲካ ፍላጎትን እሽቅድድም የተነሳ ከባለፈው አመት ሶስት እጥፍ የሚልቅ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መፈጸሙ ተገለጸ፡፡

በቀጠናው እየጎላ የመጣውን ፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ እሽቅድድም ለማሳካት የሀገራችንን የገንዘብ ተቋማት ኢላማ ያደረገ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መፈጸሙን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛዉ እንዳሉት በያዝነዉ ዓመት ካለፈዉ ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ 3 ዕጥፍ ከፍ ያለ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መደረጉን እና ከዛም መሃል ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገው በገንዘብ ተቋማት ላይ እንደነበር ገልጸዋል ፡፡

የገንዘብ ተቋማቱ በዉስጣቸው ከግለሰብ እስከ መንግስት ደረጃ ያሉ መረጃዎችን የያዘ ና ከፍተኛ ሃብት ያለበት በመሆኑ በተደጋጋሚ ሙከራዎች እንዲካሄዱበት ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና አምራች ተቋማት ሌሎች ጥቃቱ የተሞከረባቸዉ ተቋማት መሆናቸዉንም ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ ለማሳያነት በ2012 እና 2013 የነበረዉን የሳይበር ጥቃት ሙከራ ቁጥሮች በማንሳት በያዝነዉ ዓመት ግን በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩን ይናገራሉ፡፡

በ 2012 ዓ.ም 1800 ፣ በ 2013 ደግሞ 1980 የሚሆኑ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መካሄዳቸዉን እና በ 2014 ዓ.ም ግን በ 3 ዕጥፍ አድጎ 3406 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተካሂደዋል ብለዋል፡፡

ዋነኛዉ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደዉ ቀጠናዉ ላይ ያለ የፖለቲካ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ እሽቅድድም መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ፤ የፖለቲካ ፍላጎታቸዉን ለማሳካት ሲስተሞችን ሰብሮ መግባት ፣ አገልግሎቶችን እንዲቋረጡ ማድረግ እና ጥቃቶችን መፈጸም አላማቸዉ መሆኑ ነዉ የተነገረዉ፡፡

ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ደግሞ ሌሎች ምክንያት ሲሆኑ ባለፈዉ ዓመት የተጀመረዉ የህግ ማስከበሩ ስራ ፣ 6ኛዉ ሃገራዊ ምርጫ እና የህዳሴ ግድቡ የዉሃ ሙሌት የፖለቲካ ጥቅማቸዉን ለማስጠበቅ በሚሞክሩ አካላት በተደጋጋሚ ጥቃቶች እንዲሰነዘሩ ምክንያቶች ሆነዋል፡፡

ጥቃቶቹ ደርሰዉ ቢሆን ኖሮ በርካታ ኪሳራ ያደርሱ እንደነበር ሲገለጽ የሳይበር ጥቃትን መከላከል ለኤጀንሲዉ ብቻ የሚተዉ ነገር ባለመሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ግንኙነቶችን በማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ሳይበርኛ በተሰኘው መርሃግብር ላይ ገልጸዋል፡፡

በተቀናጀ ስራም ከተሞከሩት ጥቃቶች 96 በመቶ የሚሆኑትን ማክሸፍ መቻሉን ዶ/ር ሹመቴ ግዛዉ ተናገረዋል፡፡

እስከዳር ግርማ
ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *