የእግር ኳሳችን ትንሳኤን ለማረጋገጥ ዝግጁ ነኝ ሲሉ አቶ መላኩ ፈንታ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያን እግር ኳስ ትንሣኤን እውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አቶ መላኩ ፈንታ ተናገሩ፡፡
የአማራ ክልልን በመወከል ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትነት እየተወዳደሩ ያሉት አቶ መላኩ ፈንታ፣ የለውጥ ሃሳብና ተነሳሽነት በአመራርነት ለማቀጣጠል፣ከፊት ሆኖ ለምራትና ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ የመንግስት እና የግል መስሪያ ቤቶች ያካበቱትን ከፍተኛ ልምድና ውጤታማ ተሞክሮ በእግር ኳሱ መድረክ ለመጠቀምና በለውጥ ሃሳብ ትግበራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለማሳደግ እስራለሁ ብለዋል አቶ መላኩ ፈንታ፡፡
ስፖርት በተለይም እግር ኳስ የሕዝብ ፣ ለሕዝና በሕዝብ የሚከወን እንደመሆኑ በተቋማዊ ለውጥ ትግበራ የሚፈለገው ተጨባጭ ውጤት እንዲገኝ ጠንክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

በአዝጋሚ ሂደቶች በተገኙና በሚገኙ አንዳንድ ውጤቶች በመርካት ሳይሆን ሁለንተናዊ የሆነ ተቋማዊ ለውጥ ማካሄድ እንደሚፈልጉም ነው የተናገሩት፡፡
የመልካም አስተዳደር እጦት ፣ በተለይም የሙስና ችግር የስፖርቱ ውድቀት ዐብይ ምክንያት በመሆኑ መልካም አስተዳደርንና ተጠያቂነትን ማስፈን ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ለስፖርቱ እድገት ቀጣይነት አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዲኖር ስፖርቱን በቢዝነስ መርህ መምራት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት አቶ መላኩ፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመጥኑ ፣ ከእግር ኳስ ታሪካችንና ወዳድነታችን ጋር የሚጣጣሙ ፤ በዓለም አቀፍ መለኪያዎችም ምቹና ብቁ የሆኑ ስታዲየሞችንና የእግር ኳስ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት የኢትዮጵያ ስም ወደ ነበረችበት መመልስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *