የ98 አመቱ አንጋፋው የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ፣የአሁኑ እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ስያሜውን ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሊቀይር መሆኑን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል።
የኮሌጁ ምክትል ዲን አቶ በላይ ከፋለ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፣ታሪካዊ ስሙን ለማስመለስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብልዋል።
የትምህርት ቤቱ የቀድሞው ምሩቃን ኮሚቴ አዋቅረው፣ኮሌጁ በቀድሞው ስሙ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እንዲጠራ እየጠየቁ መሆኑን አቶ በላይ ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት በኋላ አንድ ክፍለ ዘመን የሚሞላው ይህ አንጋፋ የትምህርት ተቋም መቶኛ ዓመቱን ሲያከብር በቀድሞው ስሙ እንደሚሆን ተገልጿል።
የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በ1917 ዓ.ም የተመሠረተና በደርግ ዘመነ መንግስት ወደ እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንደተቀየረም ምክትል ዲኑ አስታውሰዋል።
አሁን ያለው ስያሜ የተቋሙን ታሪክና ቦታ የማይወክል በመሆኑ የቀድሞው ስሙ እንዲመለስለት ተጠይቋል።
ኮሌጁ አሁን ላይ 11 የትምህርት መስኮችና ከ 40 በላይ ስልጠናዎችን እየሰጠ የሚገኝ አንጋፍ ተቋም መሆኑንም አቶ በላይ ነግረውናል።
ኮሌጁ ከሁለት ዓመት በኋላ መቶኛ ዓመቱን በድምቀት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት መጀመሩንም ሰምተናል።
በአባቱ መረቀ
ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም
