በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረዉ ግጭት ምክንያት የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር 11 ቢሊዮን ብር ደርሶ እንደነበር ተገለፀ።

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረዉ ጦርነት ምክንያት ብሔራዊ ባንክ የእፎይታ መመሪያ እስኪያወጣ ድረስ፣ ወደ 11 ቢሊዮን ብር የተበላሸ ብድር እንደነበረዉ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ዩሐንስ አያሌዉ አስታዉቀዋል።

በትግራይ የነበሩ ፕሮጀክቶች ከጦርነቱ በፊት በአብዛኛው ጤናማ የሚባሉ እንደነበሩ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ባንኩ 43 በመቶ የተበላሸ ብድር በነበረበት ወቅት 10 በመቶ ብቻ ድርሻ እንደነበራቸዉ ተናግረዋል።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኃላ ግን ግንኙነቱ ስለተቋረጠ ሁሉም በሚባል ደረጃ ወደ ተበላሸ ብድር ገብተዋል ብለዋል በማብራሪያቸው።

የተበላሸ ብድር የሚባለዉ ብድር መክፈያ ጊዜዉ እየተቆጠረ ሲሆን ሶስት ደረጃዎች አሉት፣ ያንን መተግበር ሳይቻል በሶስት ዓመት መክፈል ካልተቻለ ወደ ተበላሸ ብድር ዉስጥ እንደሚገባ አንስተዋል።

ከፕሪቶሪያዉ የሰላም ስምምነት በኃላ በትግራይ ያሉ ፕሮጀክቶች ያሉበትን መገምገሙን የተናገሩት አቶ ዩሐንስ፣ ብዙዎቹ ሙሉ ለሙሉ ያልተጎዱበትና ጥሩ ሁኔታ ላይ መኖራቸዉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በትግራይ ያሉ ፕሮጀክቶች 80 በመቶ ወደ ስራ የገቡና ብድር በማግኝት ወደ እንቅስቃሴ መግባታቸዉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአንድ ዓመት ከስድስት ወር የፎይታ ግዜ እንደሰጣቸዉ የሚገልፁት አቶ ዩሐንስ፣ በዚህ ዓመት ዉስጥ ባንኩም ድጋፍ እያደረገላቸዉ ወደ ጤናማ መንገድ ለማስገባት እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

ባለፈዉ ዓመት በአማራ እና አፋር ክልሎች በተመሳሳይ መንገድ ተሰርቶ በርካታ ፕሮጀክቶች ከተበላሸ ብድር ወጥተዉ ወደ ጤናማ መንገድ መግባታቸዉንም ገልፀዋል።

በአቤል ደጀኔ

ነሃሴ 02 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *