በደብረብርሃን ተጠልለው የሚገኙ ከ26 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት አደጋ ውስጥ ናቸው ተባለ::
በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የሰብአዊ ዕርዳታ በመስተጓጎሉ በደብረብርሃን ጊዚያዊ መጠለያ ካምፖች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ከ26 ሺህ በላይ ዜጎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ሰምተናል።
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የስነ ህዝብ ባለሙያና የጊዚያዊ መጠለያዎች አስተባባሪ አቶ አንተነህ ገብረእግዚአብሔር፣ግጭቱ በተፈናቃዮች ላይ ትልቅ ችግር መደቀኑን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቀዋል።
በክልሉ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ዕለት ጀምሮ፣ ለተፈናቃዮች ምንም አይነት ድጋፍ እየቀረበ አይደለም ነው ያሉት።
ከግጭቱ በፊትም በመንግስት የሚደረገው ድጋፍ የተቆራረጠ እንደነበር የገለፁት አቶ አንተነህ ፣ተፈናቃዮቹ በዋናነት ድጋፍ የሚያገኙት ከግለሰቦችና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ነበር ብለዋል።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ በክልሉ የተስተዋለው አለመረጋጋት ድጋፉ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም አድርጎታል ተብሏል።
በዚህም በጊዚያዊ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ከ 26 ሺህ በላይ ዜጎችና ከህብረተሰቡ ጋር የተቀላቀሉ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ለችግር እንዲዳረጉ ሆኗል ብለዋል አቶ አንተነህ።
ወቅቱ የክረምት ወቅት መሆኑ ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል ነው የተባለው።
መንግስት ከሶስት ወር በፊት ጀምሮ በመደበኛነት ያቀርብ የነበረውን ድጋፍ ማቋረጡን የገለፁት አስተባባሪው፣የአለም የምግብ ፕሮግራምም ድጋፍ እንዳያደርግ ፍቃድ መነፈጉንም አንስተዋል።
በመሆኑም መንግስትና የረድኤት ድርጅቶች ለእነዚህ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲደርሱ ጥሪ ቀርቧል።
በአባቱ መረቀ
ነሃሴ 11 ቀን 2015 ዓ.ም
