በአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር የ7 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፣ ከባድ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ከዓምናው መጨመሩን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግሯል፡፡
በከተማዋ በባለፈው ዓመት 441 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት ደግሞ 382 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የገለፁልን የትራፊክ ማኔጅመነት ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ የሆኑት አቶ መኳንንት እያሱ ናቸው፡፡
ለሚያጋጥሙ የትራፊክ አደጋዎች ከ80 በመቶ በላይ የአሽከርካሪዎች ሀላፊነት መሆኑን የሚገልፁት አቶ መኳንንት በተለይም ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ጠጥቶ ማሽከርከር፣ሞተር ብስክሌቶች ሄልሜት ያለመጠቀም፣ቤልት አለማሰር እና የተለያዩ የቴክኒክ ብልሽቶች አጋላጭ ሁኔታዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ኤጀንሲው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ትራፊክ ዲቪዥን እና ከብሉምበርግ ኢኒሼቲቭ ጋር በጋራ በመሆን የራዳር ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከፍጥነት ወሰን በላይ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡
የኤጀንሲው የኮሚኒኬሽ ዳይሬክተር ለጣብያችን እንደተናገሩት ከሆነ በ2015 ዓ.ም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተሸከርካሪዎች የትራፊክ ህግና ደንብን በመተላለፋቸው የቅጣት እርምጃ ተወሰዶባቸዋል ብለዋል፡፡
በሀገር ደረጃ እንኳን ያለው የተሸከርካሪ ብዛት ከ1.3 ሚሊዮን የማይበልጥ ባይሆንም አንድ ተሸከርካሪ ተደጋጋሚ የትራፊክ ደንብ ጥሰት ላይ በመገኘቱ ይህን ያህል የቅጣት ሪከርዶች ሊመዘገቡ ችለዋል ሲሉ ነግረውናል፡፡
አቤል ደጀኔ
ነሃሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም
