በከተማዋ በጊዚያዊ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የኮሌራ በሽታ በፍጥነት እየተስፋፋ ነው ተብሏል።
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የስነ ህዝብ ማለሙያና የጊዚያዊ መጠለያዎች አስተባባሪ አቶ አንተነህ ገብረእግዚአብሔር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት ፣ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች በበሽታው ተይዘዋል ብለዋል ።
አሁን ላይ የስርጭቱን መጠንና ለመቀነስና በበሽታው የተያዙትን ሰዎች ለመለየት የህክምና ባለሙያዎች እየተረባረቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
እነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች ከዚህ ቀደም በስድስት ጊዚያዊ መጠለያ ካምፖች ውስጥ የነበሩ ቢሆንም ሶስቱ መጠለያ ካምፖች የግለሰብ በመሆናቸው ባለሃብቶቹ ስለፈለጓቸው አሁን ላይ መጠለያ ካምፖቹ ወደ ሶስት ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል ተብሏል።
ይህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ በአንድ ቦታ በመኖሩ የበሽታውን ስርጭት ከፍ ያደርገዋል ነው ያሉት አቶ አንተነህ።
በመሆኑም መንግስና የረድኤት ተቋማት በሽታው እንዳይስፋፋና ተፈናቃዮቹም የምግብ ዕርዳታ እንዲያገኙ አስቸኳይ ርብርብ ያስፈልጋል ተብሏል ።
በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የሰባዊ ዕርዳታ በመስተጓጎሉ በደብረብርሃን ጊዚያዊ መጠለያ ካምፖች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ከ26 ሺህ በላይ ዜጎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ መነገሩ የሚታወስ ነው።
በክልሉ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለተፈናቃዮች ምንም አይነት ድጋፍ እየቀረበ እንዳልሆነ ሰምተናል።
በአባቱ መረቀ
ነሃሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም
