በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች እዳ በመክፈል ተጠምደዋል ተባለ፡፡

በመዲናዋ ላይ የሚገኙ ባለ ኮኮብ ሆቴሎች አብዛኛዎቹ ከገቢ ይልቅ ወጪያቸው መብዛቱ ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የሰላም እጦት በመዲናዋ ባሉ ሆቴሎች ላይም ክንዱን ማሳረፉ ነው የተነገረው፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ ሆቴሎቹ በአብዛኛው የተበደሩትን ገንዘብ እየከፈሉ በመሆናቸው ገቢያቸው እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በሃገሪቱ ካለው የሰላም እጦት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የቱሪስት ፍሰት መቀነሱ እንደ ምክንያት ያነሱት የማህበሩ ፕሬዝዳንት፣ ይህ ደግሞ በሆቴሎች ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገርም አዲስ አበባ ላይ ይደረጉ የነበሩ አለም አቀፍ ስብሰባዎች መቀነሳቸውም ሆቴሎች ገቢያቸው እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር በዚህ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር ቢያደርግም፣ ምንም አይነት ለውጥ እንዳልመጣ ገልጸዋል፡፡

የገበያው መዳከም ከዚህም በከፋ ሁኔታ ከቀጠለ፣ ሆቴሎች ከፍተኛ የሆነ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እጥረት ስለሚገጥማቸው፣ ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል ሊቸግራቸው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል፡፡

በሥራ ላይ ለመቆየትም የሆቴል ባለሀብቶች ተጨማሪ ካፒታል ለመመደብ እንደሚገደዱ የገለጹት የማህበሩ ፕሬዝዳንት፣ ይህን ማድረግ ሳይችሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ አሁን ላይ ከባድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *