በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የተባባሰውን የወባ ወረርሺኝ መቆጣጠር አለመቻሉን የትግራይ ክልል አስታወቀ፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ተባብሶ የቆየውን የወባ ወረርሺኝ መቆጣጠር እንደከበደዉ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ለኢትዮ ኤፍኤም አስታዉቋል፡፡

ትግራይ ዉስጥ የወባ በሽታ በወረርሺኝ መልክ የተከሰተዉ ከጦርነቱ በፊት ከ6 ዓመት በፊት ነበር ተብሏል።

በወቅቱም ምልክቱ እንደታየ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ተችሎ እንደነበር የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አማኑኤል ሃይለ አስታውሰዋል፡፡

ጦርነቱን ተከትሎ ወረርሺኙ ከተነሳ ከ1ዓመት በላይ ሆኖታል ያሉት ሃላፊዉ ፤2014 ሰኔ ወር ላይ ነበር ወረርሺኙ በይበልጥ የታየዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኃላፊዉ ጦርነቱ ሲጀምር ወባን ለመከላከል የምንጠቀማቸዉ መንገዶች በሙሉ በመቆማቸዉ አጎበሮችን ማዳረስ፤የኬሚካል ርጭት ማድረግ እና ወባዉ ሲከሰትም ለመመርመር እና ህክምና ለመስጠትም አልተቻለም ነበር ብለዋል፡፡

በክልሉ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መኖር ፣የትግራይ ¾ተኛዉ አከባቢ በወባ የሚጠቃ ቦታ መሆን እና የምግብ እጥረት ችግሩን አባባብሶታል ተብሏል።

በተለይም ህጻናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር አስከትሏል ብለዋል ዶክተር አማኑኤል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እና ጤና ሚኒስቴር በጋራ በመሆን ባደረጉልን የአጎበር አቅርቦት ፤የፈለግነዉን ያህል ባይሆንም 48 በመቶ ለሚሆኑ ዜጎች አጎበር ማከፋፈል ችለናል ሲሉም አክለዋል፡፡

ወባ በይበልጥ እየታየ ያለባቸዉ የተመረጡ 10 ወረዳዎች ላይ ቤት ለቤት የኬሚካል ርጭትና መድሀኒትም እየተሰጠ ነው ተብሏል።

‹‹የመመርመሪያ ዕጥረት እንደ አገርም በትግራይ ክልልም አለ ፤አሁንም የወባን ወረርሺኝን መቆጣጠር አልቻልንም ነው ያሉት።
አሁን መከላከል የቻልነዉ ከፍተኛ የሆነ ሞት እንዳይከሰት ብቻ ነዉ ሲሉም ኃላፊው ተናግረዋል።

በሽታዉን ለማቆም ከዓለም የጤና ድርጅት ፣ከሌሎች አጋር ድርጅቶች እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ተባብረንኀ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *