በ2015 ዓ.ም ከ3 ሺህ 5 መቶ በላይ ዜጎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸዉ ማለፉ ተገለፀ።

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት እንዳስታወቀዉ ባለፈዉ ዓመት ብቻ 3 ሺህ 577 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸዉ ሲያልፍ ከ10ሺህ በላይ ዜጎች ከባድና ቀላል ጉዳት እንዳጋጠማቸዉ አስታዉቋል።

በባለፈዉ ዓመት 2015 ዓ.ም በሶስት ዙር የቁጥጥር ስራ በመላዉ ሀገሪቱ ሲያከናዉን የነበረዉ ተቋሙ ከ8.2ሚሊዮን በላይ ተሽከርካሪዎች ላይ የቁጥጥር ስራ መስራቱን ዋና ስራ አስፈፃሚዉ አቶ ጀማል አባሶ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

በሀገር ደረጃ ያለዉ የተሽከርካሪ ብዛት ከ1.4 ሚሊዮን እንደማይበልጥ የሚያስረዱት ዋና ስራ አስፈፃሚዉ፣ አንድ ተሽከርካሪ ላይ በተደጋጋሚ በተደረገ ቁጥጥር 8.2 ገዳማ ተሽከርካሪ ላይ ቁጥጥር ስራ መሰራቱን ያስረዳሉ።

በዚህም በተደረገ የቁጥጥር ስራ 238 ሺህ ተሽከርካሪዎች መቀጣታቸውንም ጨምረዉ ተናግረዋል።
በትራፊክ አደጋ በቀን ቢያንስ 10 ሰዉ ህይወቱን የሚያጣበትና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ፣ በትምህርት ስርዓቱ ጭምር እንዲካተት መደረጉን አንስተዋል፡፡

የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት በክልል እና ከተማ መስተዳደር ከሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም በመንገድ ደህንነት ላይ እየሰሩ ካሉ አካላት ጋር የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ከሰሞኑ ዉይይት አድርጓል።
የሚዲያ ፎረምም የተቋቋመ ሲሆን የሚዲያ አካላት ለመንገድ ደህንነት ትኩረት ሰጥተዉ እንዲሰሩም ተጠይቋል።

በአቤል ደጀኔ

ህዳር 03 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.