ክልሎች በተለያየ ደረጃ ያሉ የመንግስት አመራሮች “አካባቢያቸውን ከሽፍቶች ማጽዳት ባለመቻላቸው”፤ የመከላከያ ሰራዊት “የመንግስት መዋቅር ስራን ደርቦ እንዲሸፍን እየተገደደ ይገኛል” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ ወቅሰዋል።
ሚኒስትሩ “የሽፍታ እንቅስቃሴ” ሲሉ የጠሩት ድርጊት እና በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ እገታዎች የሚከሰቱት፤ በክልሎች ባሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት “መሰራት ያለበት ስራ ባለመሰራቱ” መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ ከዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹን የሶስት ወራት የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ዶ/ር አብርሃም ለተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ፤ በሩብ ዓመቱ ያጋጠሙ “ችግሮች እና ፈተናዎች” በሚል ከዘረዘሯቸው ውስጥ አንዱ የመከላከያ ሰራዊት ስምሪት በየአካባቢው እንዲሰፋ መደረጉን ነው።
“የመንግስት መዋቅር ላይ ያሉ አመራሮች ህዝባቸውን በማስተባበር አካባቢያቸውን ከሽፍቶች ማጽዳት ባለመቻላቸው፤ የሰራዊታችን ግዳጅ እንዲሰፋ እና የክልል መንግስት መዋቅር ስራን ደርቦ እንዲሸፍን እየተገደደ ይገኛል” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አስፍረዋል።
ዶ/ር አብርሃም ይህንኑ ጉዳይ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅትም በድጋሚ በአጽንኦት ማንሳታቸውን የአዲስ ኢንሳይደር ዘገባ ያመለክታል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሕዳር 06 ቀን 2016 ዓ.ም
