አራት ኪሎ መነሻውን ያደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለከንቲባ ጽ/ቤት ማስገባቱን የኢትዮጰያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ገለጸ፡፡

“ጦርነት ይቁም! ሠላም ይስፈን፣ መከላከያ ሰራዊቱ ባስቸኳይ ወደ ካምፕ ይግባ!” በሚል መሪ ቃል ለህዳር 30 ፣ 2016 ዓ. ም. ታላቅ ህዝባዊ ሠልፍ ለማድረግ ነው ፓርቲው ጥያቄ ያቀረበው፡፡

በዛሬው እለት ህዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች በተፈረመ ደብዳቤ፣ ጦርነት እንዲቆም፣ መከላከያ ሠራዊቱ ከዘመተባቸው ክልሎች ወጥቶ ወደ ጦር ካምፑ እንዲመለስና ፖለቲካዊ ውይይቶች እንዲከፈቱ የሚጠይቅ ህዝባዊ የአደባባይ ሠልፍ ለማድረግ እንደሆነ ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

የኢትዮጰያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ /ኢህአፓ/ እና ሌሎች ዜጎች አስተባባሪነት የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ዙሪያ ዛሬ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ የማሣወቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ለጣብያችን ገልፀዋል፡፡

ከጣብያችን ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም እንደገለፁት ኢህአፓ እና ሌሎች ሁሉን አቀፍ ሀገር ወዳድ አባላት በመሰባሰብ በጋራ በመሆን ሀገርን የማዳን ሰልፍ መጠራቱን ነግረውናል፡፡

ህዝባዊ ሠልፉ መነሻውን አራት ኪሎ የድላችን ኃውልት አድርጎ በተለያዩ ጎዳናዎችንና አደባባዮችን በማለፍ መዳረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ የዕለቱን መልዕክት በማስተላለፍ ይጠናቀቃልም ተብሏል።

በሠላማዊ ሠልፉ ላይም ከመቶ ሺህ ሰው በላይ እንደሚጠበቅ የገለፁት አስተባባሪዎቹ፣ ለዚህ የሚሆን የፀጥታና ደህንነት የአዲስ አበባ ፖሊስ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ሠልፉ በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የጦር ሠራዊቱ ከጦርነት አውድ ውጪ የሚፈፅማቸውን ዘመቻዎችን በማቆም ወደ ጦር ሰፈሩ እንደሚለስ የሚጠይቅ መሆኑንም አስተባባሪዎቹ ለጣብያችን ተናገግረዋል፡፡

ሰላማዊ ሰልፉን ከጠሩት አስተባባሪዎች መካከልም እንደ ናትናኤል መኮንን፣የሺዋስ አሰፋ የመሣሠሉ ፖሊቲከኞችና ሌሎችም ሀገር ወዳዶች የተጠራ ነው መባሉን ኢትዮ ኤፍ ኤም ያገኘው መረጃ ያለመክታል፡፡

በአቤል ደጀኔ

ህዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *