የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ስምምነትን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔውን አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ፡፡

የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ መንግሥት ካቢኔ ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ደርሰውታል በተባለው ስምምነት ዙሪያ ለመነጋገር መሆኑን የሶማሊያ ዜና ወኪል ሶናን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ መሠረተ ልማት ድርሻ እንዲሁም እንደ ሉዓላዊት አገር እውቅና ለማግኘት የባሕር ጠረፍ ለመስጠት ትናንት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ ይታወሳል።

በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ የጦር ሰፈር እና ወደብ ለማልማት 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ተቀብላ በምላሹ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንዲሁም እንደ አገር ዕውቅና ለመስጠት ከስምምነት መድረሷ ተዘግቧል።

ሶማሊላንድ እአአ 1991 ላይ ራሷን ከሶማሊያ በመገንጠል ነጻነቷን ብታውጅም ኢትዮጵያን ጨምሮ የትኛውም አገር እስካሁን እውቅና ሳይሰጣት ቆይቷል።
ሶማሊያም ብትሆን እንደ አንድ የግዛቷ አካል የሆነች ክልል አድርጋ ነው የምትመለከታት።

ትናንት የተፈረመውም የመግባቢያ ሰነድ ግን ይህን እንደሚቀይር የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ትናንት በተካሄድ ሥነ ስርዓት ላይ ተናግረዋል።

የራስ ገዟ ሶማሌላንድ ፕሬዜዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ፤ ትናንት በነበረው የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ፊርማ ወቅት ኢትዮጵያ ከስምምነቱ በኋላ “ለሶማሊላንድ ነፃ አገርነት ዕውቅና የምትሰጥ የመጀመሪያዋ አገር እንደምትሆን” በምላሹ ደግሞ ሶማሊላንድ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር እና የባሕር ኃይል መቀመጫ እንዲኖራት በቀይ ባሕር በኩል 20 ኪሎ ሜትር የሆነ መሬት ለኢትዮጵያ በሊዝ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ግን የሶማሊላንድን የነፃ አገርነት ዕውቅና እንደምትቀበል በይፋ ባታረጋግጥም፣ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉ ሶማሊያን ሳያስቆጣ አልቀረም።

የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በማኅበራዊ ሚዲያዎቻቸው ስምምነቱ የሶማሊያን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው እያሉ ነው።

የሶማሊያ የነዳጅ እና የማዕድን ሃብት ሚንስትር እንዲሁም የሕዝብ እንደራሴ የሆኑት አብዲራዛክ ሞሐመድ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የደረሱት ስምምነት ሶማሊያን ለመከፋፈል የሚሞክር ነው ካሉ በኋላ፣ የአገራቸው ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ጥያቄ ላይ ሊወድቅ እንደማይችል በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

ሚንስትሩ ከሶማሊያ ዕውቅና ወጪ ኢትዮጵያ ከክልል መንግሥት ጋር የወደብ ኪራይ እና ወታደራዊ ጉዳይን የተመለከተ የመግባቢያ ሰነድ መፈረም አትችልም ሲሉ የመግባቢያ ሰነዱን አጥብቀው ተቃውመዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *