አንጋፋው የደቡብ ሬድዮ እና ቴሌቭዢን ድርጅት አዲስ በተደራጁ ክልሎች የጋራ በጀት እንደሚቀጥል ኢትዮ ኤፍ ኤም ከተቋሙ ሰምቷል፡፡
ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅቱ በቀድሞ የደቡብ ክልል አደረጃጀት ውስጥ የሚገኙ ዞኖች አሁን ላይ እራሳቸውን ችለው በመደራጀታቸው የመፍረስ ስጋት ውስጥ መውደቁ ሲነገር ነበር፡፡
ነገር ግን የደቡብ ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘላለም ገነሞ ተቋሙ ምንም የመፍረስ ስጋት የለበትም ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ የደቡብ ክልል ለአራት ቢከፋፈልም የሬድዮ እና ቴሌቭዥን ጣቢያው ግን በክልሎቹ የጋራ በጀት እንደሚቀጥል አቶ ዘላለም ገነሞ አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ የሲዳማ ክልልን ጨምሮ በቀድሞ የደቡብ ክልል አደረጃጀት ወስጥ የነበሩ ዞኖች የራሳቸውን ሬድዮ እና ቴሌቭዢን እየከፈቱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ይህንንም ተከትሎ አንጋፋ እና ለአከባቢው ማህበረሰብ በመረጃው ተደራሽ በመሆን የቆየው ተቋም ከበጀት እጥረት እና በተለያዩ ምክኒያቶች የመፍረስ ስጋት ውስጥ መግባቱን የቀድሞ እና የአሁን የጣቢያው ጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ ይህን ቢሉም የድርጅቱ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘላላም አራቱም ክልሎች በጀት በመመደብ ጣቢያውን በጋራ የማስተዳደር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አንስተዋል፡፡
በመሳይ ገብረ መድህን
ታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም
