የኢትዮጵያ መንግስት ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀዉ 41 የአልሸባብ ቡድን አባላት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
ፍርዱ ከተላለፋቸው መካከል የወታደራዊ መሪዉ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል ነዉ የተባለዉ፡፡
ብይኑን የሰጠዉ በድሬዳዋ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ምድብ ችሎት ሲሆን፤ ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክር አላቀረቡም በሚል የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ናቸው፡፡
ሁሴን አልመድ/ኤሊያስ ሁሴን/ የመጀመሪያ ተከሳሽ ሲሆን፤ እንደ መንግስት ገለጻ ከሆነ ለአሸባሪዉ ቡድን እንደ መሪ ሆኖ ሲሰራ ነበር፡፡
ሁለተኛዉ ተከሳሽ ኢብራሂም ጂብሪል የሚባል ሲሆን የበታች ወታደራዊ መሪ ነበር ተብሏል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ጉዳዮች ክፍል ዳይሬክቶሬት ጄኔራል 57 ምስክሮችን እንዲሁም 3መቶ96 የጽሁፍ ማስረጃዎችን ከተመለከተ በኋላ በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ መስርቶባቸዉ ነበር፡፡
ሁሉም 41 ተከሳሾች ከ2019 ጀምሮ ሶማሊያ የሚገኘዉ የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን አባላት ናቸዉ ያለ ሲሆን፤ ልምምዳቸዉን ካጠናቀቁ በኋላ በ2021 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተፈጸመ ጥቃት ተሳታፊ ነበሩ ብሏል፡፡
በአፍዴር ዞን የተለያዩ አከባቢዎች በስፋት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ደርሼበታለሁ ያለዉ ዳይሬክቶሬቱ፤ በኢትዮጵያ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በማሰብ አብዛኛዎቹ የጦር መሳሪያዎችን ጭምር ሲያቀርቡ ነበር ነዉ ያለዉ፡፡
በወቅቱም 2መቶ65 ንጹህን ዜጎች ህይወታቸዉ ሲያልፍ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል አባላትን ጨምሮ 3መቶ23 ሌሎች ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚገልጸዉ ደግሞ 13 ሚሊየን 5መቶ ሺህ የሚደርስ የኢትዮጵያ ብር የንብረት ዉድመት ደርሷል ነዉ የተባለዉ፡፡
ተከሳሾቹ ከሽብርተኝነት ወንጀል በተጨማሪ ደግሞ የአልሸባብ ቡድን አባላት በመሆናቸዉም ጭምር ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
መንግስት እንደሚለዉ ከሆነ ተከሰሾቹ 5ጊዜ የመከላከያ ምስክር እንዲያቀርቡ ዕድል ተሰጥቷቸዉ ነበር፡፡
የቡድኑ መሪ ሁሴን አልመድ የዕድሜ ልክ እስራት ሲፈረድበት፤ 19 ተከሰሾች 11 እና 12 አመት ያለ ይግባኝ፤ 8 ተከሳሾች 8 እና 9 ዓመት እንዲሁ ያለ ይግባኝ እና ቀሪ 10 ተከሰሾች ደግሞ 7 እና 8 ዓመት ያለ ይግባኝ ተፈርዶባቸዋል፡፡
እስከዳር ግርማ
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
