የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰላማዊ ተቃዉሞችን የሚያቀርቡ ፓለቲከኞችን እንዲሁም ጋዜጠኞችን ያለ ፍርድ ለማሰር ተጠቅሞበታል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጿል፡፡
በአማራ ክልል እየተካሄደ የሚገኘዉን የትጥቅ ግጭት ተከትሎ ለስድስት ወራት በትግበራ ላይ የነበረዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 24 ባደረገዉ ልዩ ስብሰባዉ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ባለፉት 6 ወራት ጊዜ ዉስጥም መንግስት ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም ተጠርጣሪዎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር፣ ገደቦችን ማስቀመጥ፣ የመንቀሳቀስ መብትን መገደብ እንዲሁም የህዝብ ስብሰባዎችንም ሆነ ሰላማዊ ሰልፎችን እንዲከለክል ሆኗል ሲል ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት መሰረታዊ መብቶችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም የሚገድብበትን ኋላ ቀር አሰራር ማቆም አለበት ሲልም አሳስቧል፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊያን በአማራ ክልል የቀጠለ ግጭት እያስተናገዱ ነዉ፤ በትግራይ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀዉስ አለ፤ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከባድ የደህንነት ስጋት እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ የተንሰራፋ ችግር ባለበት በዚህ ወቅት የአገሪቱ መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም መሰረታዊ መብቶችን መገደብ ማቆም አለበት፤ የሚዲያዉ ሚና እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ዛሬም እንደሁልጊዜዉ አስፈላጊ ነዉ›› ሲሉ ቲገር ቻጉታህ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡
ለ 4ወራት የተራዘመዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስካሁን ድረስ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ አልታተመም ያለዉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ይህም መረጃን የማግኘት መብትን እንዲሁም የህጋዊነት መርህን የሚጥስ ነዉ ሲል ገልጾታል፡፡
ዜጎችም እንቅስቃሴያቸዉ በህግ እንደሚዳኝ አልያም አዋጁ በመላዉ አገሪቱ የሚተገበር መሆኑን እና አለመሆኑንም ለማወቅም አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል ነዉ ያለዉ፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቤተሰቦቻቸዉን አነጋግሬያለሁ ሲል ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሰረት 5 ፖለቲከኞች እና 3 ጋዜጠኞች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር ያለምንም ክስ በእስር ላይ ይገኛሉ ፡፡
እስከዳር ግርማ
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም
