ጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ሱዳን መግባታቸው ተገለፀ

ጠ/ሚንስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ሱዳን መግባታቸው ተገለፀ፤ ጠ/ሚንስትሩ ያቀኑት የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት ጊዜያዊ መቀመጫ ወደ ሆነችው ፖርት ሱዳን መሆኑን ከጽ/ቤታቸው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

“ጉዞው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሱዳን መረጋጋት የሚያከናውኑት ጥረት ቀጣይ ርምጃ ነው” ሲል ጽ/ቤቱ አስታውቋል።

ጠ/ሚኒስትር አብይ ባሳለፍነው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ስለ ሱዳን ጉዳይ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል “ከሁለቱ ተዋጊ ሃይሎች ገለልተኛ ሆነን ችግራቸው በሰላም እንዲፈታ ጥረት ስናደርግ ነበር” የሚለው ይገኝበታል።

ጦርነቱን ተከትሎ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫቸውን ከካርቱም ወደ ወደ ፖርት ሱዳን መቀየራቸው ይታወቃል።

የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር ሌተናል ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት 15ኛ ወሩን ማስቆጠሩ ይታወቃል።

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች የዘር ማጽዳት እና የጦር ወንጀል ተፈጽሟል የሚሉ ውንጀላዎች እየቀረበባቸው ይገኛል።

ሐምሌ 02 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *