ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ለግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ለመጠቀም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዢ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ መፈረማቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በዚህም በሁለቱ ሀገራት ለሚደረግ ግብይት የራሳቸውን ገንዘብ ማለትም ድርሃምና ብር ለመጠቀም ከስምምነት የደረሱ ሲሆን ሁለቱ አካላት ለተግባራዊነቱ ምቹ መደላድል ለመፍጠር ጥረት እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የኢትዮጵያ አንዷ የንግድ አጋርና የውጪ ኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗን ገልጸው ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርገዋል ብለዋል።

በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ቀጣይነት ያለው ልማትና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ብሔራዊ ባንክ ገዥ ካሊድ ሞሃመድ ባላማ በበኩላቸው ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ መምጣታቸውን እንደሚያሳይ አመላክተዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሐምሌ10 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *