በተፈጥሮ አደጋ ወቅት በተለይም ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸውም ሲል ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ በገዜ ጎፋ ወረዳ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ የደረሰው የመሬት ናዳ አደጋን ተከትሎ በሰዎች ሕይወት ላይ፣ በመኖሪያዎቻቸው እና በመተዳደሪያዎቻቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የሚደርሱት ጥቆማዎች እና ሪፖርቶች በእጅጉ አሳሳቢ መሆናቸዉን አስታዉቋል፡፡
የጎፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባሳወቀው መሠረት ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ከ229 በላይ ሰዎች መሞታቸውን፣ 81 የሚሆኑትም ሴቶች መሆናቸውን፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በአካባቢው ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ሲል መግለጹን አስታዉቋል፡፡
ነገርግን የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል እና የአፋጣኝ ምላሽ ሥራው እንደሚቀጥልም ነዉ አክሎ የገለጸዉ፡፡
በደቡብ ክልል እና በዞኑ የመንግሥት አካላት ትብብር፣ በሀገራዊ የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በአካባቢው ነዋሪዎች በወረዳው በድንገተኛ የናዳ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተወሰነ አፋጣኝ ድጋፍ መደረጉ አበረታች ነዉ ያለዉ ኢሰመኮ፤
ሆኖም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰንዳይ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ማዕቀፍ ፣ በአፍሪካ ሕብረት የሰንዳይ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ ማዕቀፍ የተግባር መርኃ ግብር እና በብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ መሠረት የሰብአዊ መብቶች መርሖችን እና ድንጋጌዎችን የሚያሟላ እንዲሆን ለማስቻል የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት እና ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርጉ ኢሰመኮ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት አሳሳቢነት በማስታወስ “በተፈጥሮ አደጋ ወቅት በተለይም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአረጋውያን እና በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ከግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ፣ በዚሁ ክስተት ሳቢያ ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የተጠለሉ ሰዎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግላቸው” ጥሪ አቅርበዋል።
በእስከዳር ግርማ
ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም
