የ”ግድቤን በደጄ”ፕሮጀክት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ቆላማ ፣ ከፊል ቆላማና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች በስፋት ይተገበራል ብለዋል ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፡፡
ከ4 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚደርገው “ግድቤን በደጄ” ፕሮጀክት በ5 ቢሊየን ብር ወጭ ለ5 ዓመታት የሚተገበር ሲሆን በሀገሪቱ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ከቧንቧ ውሃ በተጨማሪ የዝናብ ውሃን በማሰባሰብ ዜጎችን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
“ግድቤን በደጄ” በሱማሌ ክልል፤በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤በሀረሪ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት ትምህርት ቤቶች ግንባታ መከናወኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በሌሉች ክልሎችም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
በውሃ ችግር ምክንያት የሚከሰቱ የመማር መስተማር ችግሮችን በመፍታት የተረጋጋ የመማር ማስተማር ስርዓት እንዲፈጠር ፤የወጣቶች ፤የሴቶች የስራ እድል ከማስፋት አኳያም ሆነ ለአካባቢው አርብቶ አደሮች ለከብቶቻቸው ያለድካም ውሃ እንዲያገኙ በማስቻል በውሃ ምክንያት የሚከሰት ግጭትንም እንደሚቀንስም ተነግሯል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ “ግድቤን በደጄ” ዜጎችን በመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በኢነርጂ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እና ጽዱ ሀገርና አካባቢ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት አማካኝነት ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በሀገሪቱ የተመረጡ አካባቢዎች 81 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት ያለውን የውሃ ችግር በመቀነስ የተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጥ በውሃ እጥረት ምክንያት እንዳይስተጓጎል ማድረግ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
ከመጠጥና ንጽህናን ከመጠበቅ ባለፈ የሚኖረውን ትርፍ ውሃ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግም አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የውሃ አማራጭ የሌላቸው፣ ዝናብ አጠር የሆኑና ችግሩ በስፋት የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች ቅድሚያ ይሰጣል ያሉት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በ5 ዓመቱ የፕሮጀክት ማስፋፋት ሂደት 4.8 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከ5ቢሊየን ብር በላይ ወጭ ይደረግበታል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ትምህርት ቤቶች ላይ ሲተገበር ተማሪዎች ውሃ ለመቅዳት ከ2 እስከ 4 ሰዓት የሚሄዱበትን ድካም ከመቀነስ ባሻገር በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ብለዋል።
ይህ ብቻ አይደለም የ”ግድቤን በደጄ”ፕሮጀክት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ቆላማ ፣ ከፊል ቆላማና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች በስፋት ይተገበራል ሲሉም ያክላሉ፡፡
በያይኔአበባ ሻምበል
ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም
