የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በተከበበው የጋዛ ሰርጥ እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምታደርገውን ርህራሄ የለሽ ጦርነት ‹‹ተቀባይነት የሌለዉ ነዉ›› ሲሉ አውግዘዋል።
በዚሁ ሁኔታ ህብረቱ ከእስራኤል ጋር በትብብር መቀጠል አይችልም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እስራኤል ታሪክን እንደፈለገች ልትተረጉም ትችላለች፤ነገርግን የአለም አቀፍ ህግን ማክበር ደግሞ አስገዳጅ ነዉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ትብብራችን መቀጠል አይችልም ሲሉ ቦሬል ተናግረዋል።
በጋዛ ውስጥ የምናየው የሰብአዊ ጥፋት ሰው ሊቋቋመዉ የማይችለዉ ነዉ ያሉት ሃላፊዉ፤ 17ሺህ ወላጅ አልባ ልጆች ሲኖሩ ወደ 40ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል፡፡ ጋዛን እንደገና ለመገንባት እና ፍርስራሹን ለማውጣት 10 ዓመታት ያስፈልጋቸዋል ሲሉም አክለዋል፡፡
በተጨማሪም ቦሬል እስራኤል በፍልስጤም ግዛት ውስጥ መኖሯ ህገወጥ ነው ፡፡ በተቻለ ፍጥነት መቆም አለበት የአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ብይን ተግባራዊ ለማድረግም የአውሮፓ ህብረት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ከጥቅምት 7 ጀምሮ ከ39ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ስትገድል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አቁስላለች።
በተጨማሪም ሁለት ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸዉን የሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገባ ያመለክታል፡፡
በሊዲያ ደሳለኝ
ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም
